ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ባይደን ስልጣን ከማስረከባቸው በፊት ለዩክሬን ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አጸደቁ
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለዩክሬን የሚሰጠውን ድጋፍ ለማቆም መወሰናቸው ይታወሳል
አሜሪካ ለዩክሬን የሰጠችው ገንዘብ ከ60 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ባይደን ስልጣን ከማስረከባቸው በፊት ለዩክሬን ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አጸደቁ፡፡
ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ ልዩ ዘመቻ በሚል የተጀመረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት አንድ ሺህ ቀን ያለፈው ሲሆን አዳዲስ ክስተቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።
ዩክሬን በሩሲያ የተቃጣባትን ጦርነት በበላይነት ለመቋጨት በአሜሪካ አስተባባሪነት በርካታ ሀገራት የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ከ20 ቀናት በኋላ ስልጣን ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደሚያስረክቡ የሚጠበቁት ፕሬዝዳንት ባይደን የመጨረሻ ዙር ድጋፍ ማጽደቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ስልጣናቸውን ከማስረከባቸው በፊት የ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ያጸደቁ ሲሆን ዩክሬን በሩሲያ ላይ ጥቃት ማድረስ እንድትችል የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን አድርገዋል፡፡
በሁለት መንገድ ለዩክሬን ይሰጣል የተባለው ይህ ድጋፍ የመጀመሪያው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ዘመናዊ ጦር መሳሪያዎች ከአሜሪካ ጦር መጋዝኖች ለዩክሬን በቀጥታ ተላልፈው እንዲሰጡ የሚልም ይገኝበታል፡፡
በአጠቃላይ አሜሪካ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ለዩክሬን የሰጠችው ድጋፍ ከ61 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር በ100 አመታቸው ህይወታቸው አለፈ
ከሁለት ወር በፊት በተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን የሚሰጠው የአሜሪካዊንን ገንዘብ አስቆማለሁ ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ጦርነቱን በድርድር እንዲቋጭ አደርጋሉ የሚሉት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት ጉዳዩን የሚመራ ቡድንም አቋቁመዋል፡፡
ትራምፕ የቀድሞው የአሜሪካ ጦር ጀነራል ኬዝ ኬሎግን የዩክሬን ሰላም ቡድንን እንዲመሩላቸው ሾመዋል፡፡
ቡድኑ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ወደ ኪቭ እና ሞስኮ አቅንቶ ከሁለቱ ሀገራት መሪዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርግ መናገሩ አይዘነጋም፡፡