እስራኤል የአሜሪካውን "ታድ" የሚሳኤል መቃወሚያ ስርአት መጠቀም ጀመረች
የሚሳኤል መቃወሚያው ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው የሃውቲዎችን ባለስቲክ ሚሳኤልን መትቶ ለመጣል ነው
1 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣው ስርአት ለአንድ ጊዜ ሚሳኤል ማክሸፍ 10 ሚሊየን ዶላር ወጪ ይጠይቃል ተብሏል
እስራኤል የአሜሪካውን "ታድ" የሚሳኤል መቃወሚያ ስርአት መጠቀም ጀመረች።
የእስራኤል ጦር እንደዘገበው በምህጻሩ "ቲኤችኤኤዲ" የተሰኘው የሚሳኤል መቃወሚያ ስርአት በትናንትናው እለት ከየመን የሃውቲ ታጣቂዎች የተተኮሰ ባለስቲክ ሚሳኤልን መትቶ ለመጣል ውሏል።
አሜሪካ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትዕዛዝ "ታድ"ን ወደ እስራኤል የላከችው በጥቅምት ወር 2024 ነበር።
ዋሽንግተን ባለስቲክ ሚሳኤሎችን በማምከን የሚታወቀውን ስርአት ለአጋሯ ቴል አቪቭ የላከችው ኢራን ከ200 በላይ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ከተኮሰች ከ12 ቀናት በኋላ ነው።
በሎክሄድ ማርቲን ኩባንያ የሚመረተው "ታድ" በምድር ከባቢ አየር ውስጥ እና ከ30 እስከ 150 ኪሎሜትር ከፍታ የሚምዘገዘጉ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን አድኖ በመምታት ይታወቃል።
ከእስራኤል "አሮው 2" እና "አሮው 3" በተሻለ ሚሳኤሎችን መትቶ የመጣል አቅም እንዳለውም ይነገርለታል። ይህ የሚሳኤል መቃወሚያ ስርአት በአሜሪካ ጦር ብቻ ጥቅም ላይ ሲውል የቆየ ነው። የአሜሪካ ጦር ሰባት "ታድ" እንዳለው መረጃዎች ያመላክታሉ።
እስራኤል "አሮው"፣ "አይረን ዶም" እና "ዴቪድ ስሊንግ" በተሰኙና ከአሜሪካ ጋር በትብብር በሰራቻቸው መሳሪያዎች ነው የሚቃጡባትን የሚሳኤል ጥቃቶች ስታከሽፍ የቆየችው።
ይሁን እንጂ ቴል አቪቭ የምትተማመንበትና ዋጋው ውድ ነው የሚባልለት "አሮው" ከአንዴም ሁለቴ ከየመን የሃውቲ ታጣቂዎች የሚተኮሱ ሚሳኤሎችን ማክሸፍ ተስኖት ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።
የእስራኤል ጦር በእስራኤል ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው የአሜሪካው "ታድ" የአየር መቃወሚያ ስርአት ከየመን የተተኮሰ ሚሳኤል የእስራኤል የአየር ክልል ሳይገባ መትቶ መጣሉን ገልጿል።
ጦሩ ይህን ይበል እንጂ የሃውቲዎችን የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ሽሽት ሚሊየኖች በምድር ውስጥ መደበቂያዎች እንዲገቡ የማስጠንቀቂያ ድምጽ ያለማቋረጥ ሲሰማ እንደነበር ተዘግቧል።
በቤን ጉሪን አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያም በረራዎች ለ30 ደቂቃዎች መራዘማቸውን ነው የእስራኤል ብሮድካስት ባለስልጣን ያስታወቀው።
እስራኤል በየመን የምትፈጽመውን ድብደባ ያጠናከረች ሲሆን፥ ሃውቲዎችም እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመው "የዘር ጭፍጨፋ" እስካልቆመ ድረስ የሚሳኤል ጥቃቱ ይቀጥላል ሲሉ ዝተዋል።
ከ150 እስከ 200 ኪሎሜትሮች ድረስ በመጓዝ ሚሳኤል የሚያከሽፈው "ታድ" የእስራኤላውያንን ስጋት ይቀንሳል ተብሎ ታምኖበታል።
የአጭር፣ መካከለኛ እና ረጅም ርቀት ተመዘግዛጊ ሚሳኤሎች መቃወሚያ ስርአቱ በተለይ የባለስቲክ ሚሳኤሎችን በመምታት ውጤታማነቱ ቢነገርለትም ዋጋው ግን ከፍተኛ ነው።
1 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣው ስርአት ለአንድ ጊዜ ሚሳኤል ማክሸፍ 10 ሚሊየን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅ ተገልጿል።