አሜሪካ ባለ ነጭ ጭንቅላቱን ንስር ወፍ ብሔራዊ ምልክት እንዲሆን ወሰነች
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለ ነጭ ቀለሙ ንስር የአሜሪካ ምልክት እንዲሆን በፊርማቸው አጽድቀዋል
ሀገሪቱ እስካሁን ቀስት የያዘ ንስር እንደ ብሔራዊ ምልክት አድርጋ ስትጠቀም የቆየች ቢሆንም በይፋ ሳይታወጅ ቆይቷል
አሜሪካ ባለ ነጭ ጭንቅላቱን ንስር ወፍ ብሔራዊ ምልክት እንዲሆን ወሰነች፡፡
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ እንደ ሀገር ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ ብሔራዊ ምልክት አልነበራትም፡፡
ሀገሪቱ ከተመሰረተችበት ከ1782 ጀምሮ ከአንገት በላይ ነጭ ቀለም ያለው ንስርን እንደ ብሔራዊ ምልክቷ ለመጠቀም የሞከረች ሲሆን የህግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ግን በይፋ የጋራ አቋም ባለመያዛቸው ሳይሳካ ቆይቷል፡፡
ቶማስ ጄፈርሰን እና ጆን አዳምስ ይህን ንስር እንደ ብሔራዊ ምልክት ለማድረግ ያደረጉት ጥረትም ሳይሳካ የቀረ ሲሆን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እስኪፈርሙ ድረስ ሀገሪቱ በጥፍሮቹ ቀስት የያዘ ንስርን እንደ ብሔራዊ መገለጫ ሲጠቀሙ ቆይተዋል፡፡
ስልጣን ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለማስረከብ ጥቂት ቀናት የቀራቸው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ይህ ከአንገቱ በላይ ነጭ ቀለም ያለውን ንስር በይፋ የአሜሪካ ብሔራዊ ምልክት እንዲሆን አጽድቀዋል ሲል ኤንቢሲ ዘግቧል፡፡
ፕሬዝዳንቱ መፈረማቸው የተሰማው የአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ባለ ነጭ ቀለም ንስርን ብሔራዊ ምልክት እንዲሆን ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ነው፡፡
አዲሱ አርማ በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሰንደቅ አላማ ላይ፣ አንድ ዶላር ላይ፣ ወታደራዊ አርማዎች እና ሌሎች ብሔራዊ ምልክቶች ላይ ይታተማልም ተብሏል፡፡
የአሜሪካ አባት በመባል የሚታወቁት ቤንጃሚን ፍራንክሊን ይህን ከአንገት በላይ ነጭ ቀለም ያለው ንስር የመጥፎ ምግባር ምልክት ነው በሚል ብሔራዊ አርማ እንዳይሆን ተቃውመው እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡