ዝነኛ የሆሊውድ ተዋናዮች ፕሬዝዳንት ባይደን ከምርጫው ራሳቸውን እንዲያገሉ ይፈልጋሉ ተባለ
ለፓርቲው ምርጫ ቅስቀሳ ሊለገስ የነበረ 90 ሚሊዮን ዶላር ፕሬዝዳንቱ ራሳቸውን ካላገለሉ እንደማይለቁ ገልጸዋል
በጫና ውስጥ ያሉት ፕሬዝዳንት ባይደን "የትም አልሄድም ፣እናሸንፋለን" ብለዋል
ዝነኛ የሆሊውድ ተዋናዮች ፕሬዝዳንት ባይደን ከምርጫው ራሳቸውን እንዲያገሉ ይፈልጋሉ ተባለ።
የፊታችን ህዳር ወር ላይ ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አነጋጋሪነቱ እንደቀጠለ ይገኛል።
ፕሬዝደንት ባይደን ባለፈው ወር የሪፐብሊካን ተወካይ ከሆኑት የቀድሞ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በነበረው ክርክር ደካማ አፈጻጻም በማሳየታቸው ምክንያት በድጋሚ ለመመረጥ ባላቸው እድል ላይ የራሳቸው የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ጭምር ጥርጣሬ ውስጥ ገብተዋል።
ዝነኛው የሆሊውድ ፊልሞች ተዋናይ ጆርጅ ኩልኒንን ጨምሮ ከ10 በላይ የዲሞክራት ፓርቲ ደጋፊ የፊልም ባለሙያዎች ፕሬዝዳንት ባይደን ከምርጫው ራሳቸውን እንዲያገሉ እንደሚፈልጉ ተገልጿል።
እንዲሁም የፓርቲያቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ አባላት እና ከፍተኛ አመራሮችም ፕሬዝዳንት ባይደን በምርጫው ከቀጠሉ የሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ በከፍተኛ ብልጫ ሊመረጡ ይችላሉ ብለው ስጋት አላቸው ተብሏል።
እንደ ኒዮርክ ታየምስ ዘገባ ከሆነ አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ ተቋም ለዲሞክራት ፓርቲ ምርጫ ቅስቀሳ በሚል ሊለግሰው የነበረውን 90 ሚሊዮን ዶላር ፕሬዚዳንት ባይደን ከምርጫው ራሳቸውን እስከሚያገሉ ድረስ ገንዘቡን እንደማይለቅ አስታውቋል።
ባይደን ከውድድሩ ገለል እንዲሉ ጫና ቢደረግባቸውም፣ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ትክክለኛ እጩ አሳቸው እንደሆኑ እየተናገሩ ናቸው።
ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት "እኔ የትም አልሄድም፣ በምርጫው እቆያለሁ ደሞም እናሸንፋለን" ብለዋል።
የወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ፣ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ባለቤት ሚሼል ኦባማ እና የካሊፎርኒያ ገዢው ጋቪን ኒውሶም ባይደንን ሊተኩ ይችላሉ ተብለው ተጠብቀዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ የዓለማችን ባለጸጋ የሆነው ኢለን መስክ ለዶናልድ ትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ገቢ ለሚያሰባስብ ቡድን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።