በኡጋንዳ አባትነታቸውን ለማረጋገጥ የዘረመል ምርመራ የሚያደርጉ ወንዶች ቁጥር ጨምሯል ተባለ
በኡጋንዳ አንድ ግለሰብ ካሉት 25 ልጆቹ ውስጥ 10ሩ ከእሱ እንዳልተወለዱ ተገለጸ
የምርመራ ፍላጎት መጨመሩ በርካታ ትዳሮች ሊፈርሱ እና ልጆች ሊጎዱ እንደሚችሉ ተሰግቷል
በኡጋንዳ አንድ ግለሰብ ካሉት 25 ልጆቹ ውስጥ 10ሩ ከእሱ እንዳልተወለዱ ተረጋገጠ።
በኡጋንዳ አንድ ባለጸጋ ካሉት 25 ልጆች መካከል 10ሩ የእሱ እንዳልሆኑ በዘረመል አልያም ዲኤንኤ ምርመራ መረጋገጡ ብዙዎችን አስገርሟል።
የምርመራ ሪፖርቱን ተከትሎም የዲኤንኤ ምርመራ የሚያደርጉ አባቶች ቁጥር መጨመሩ ተገልጿል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ የዲኤንኤን ምርመራ የሚያደርጉ ሰዎች መጨመሩን ተከትሎም በርካታ ትዳሮች ፈርሰው ልጆች እንዳይጎዱ ተሰግቷል።
በወለዳቸው ልጆች ጥርጣሬ የገባው አንድ በኡጋንዳ የሚኖር እስራኤላዊ የስድስት ወር ልጁ የእሱ እንዳልሆነ በምርመራ ካረጋገጠ በኋላ ሚስቱን መግደሉ ተገልጿል።
በድርጊቱ ግራ የተጋባው የሀገሪቱ የልማት ሚንስትር እንዳሉት "ያልሆነ ጥርጣሬ ውስጥ በመግባት የቤተሰባችሁን ህይወት አደጋ ውስጥ አትጣሉ፣ እንደ አያቶቻችን ብንኖር ይሻላል" ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኡጋንዳ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚንስቴር ቃል አቀባይ በበኩላቸው በየዕለቱ ቢያንስ 100 ሰዎች የዲኤንኤ ምርመራ ጥያቄ ለመንግሥት ሆስፒታሎች በማቅረብ ላይ ናቸው ብለዋል።
የገበያውን መድራት የተረዱት የግል ክሊኒኮች የዲኤንኤን ምርመራ እንደሚያደርጉ ማስታወቂያ በማስነገር ላይ እንደሆኑም ተገልጿል።
የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚንስቴርም ጥራታቸውን ያልጠበቁ የላብራቶሪ ግብዓት በህገወጥ መንገድ ሊገቡ እንደሚችሉ እና ለቤተሰብ መበተን ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉም አስጠንቅቋል።
ሚንስቴሩ አክሎም የዲኤንኤን ምርመራ ለማድረግ ያሰቡ ወላጆች መጀመሪያ የስነ ልቦና ምክር አገልግሎት ማግኘት እንደሚገባቸውም ምክረ ሀሳቡን አቅርቧል።