ፕሬዝዳንት ቻኩዌራ በቀድሞ የእንግሊዝ ቅኝ ተገዢ ሀገራት መድረክ ላይ እንደማይሳተፉ ተናግረዋል
የማላዊ ፕሬዝዳንት ወጪ ለመቆጠብ ሲሉ የውጭ ሀገራት ጉዟቸውን ሰረዙ፡፡
የቀድሞ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሀገር የሆነችው ማለዊ ወጪ ለመቆጠብ ስትል የውጭ ሀገራት ጉዞዎችን ሰርዛለች፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ላዛረስ ቻኩዌራ በሩዋንዳ አስተናግጅነት በሚካሄደው ኮመን ዌልዝ ወይም የቀድሞ እንግሊዝ ቅኝ ተገዢ ሀገራት ጉባኤ ላይ እንደማይሳተፉ አስታውቃለች፡፡
ፕሬዝዳንቱ በዚህ ጉባኤ ላይ እንደማይሳተፉ የገለጹት ወጪ ለመቆጠብ ሲሆን በዚህም ሀገሪቱ 261 ሺህ ዶላር እንደምታተርፍ ገልጻለች፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ቻኩዌራ በኦስትሪያ ቬና በሚካሄደው የዓለም ነዳጅ ላኪ ሀገራት ጉባኤ ላይ እንደማይሳተፉ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የማላዊ ፋይናንስ ሚኒስትር በበኩላቸው መንግስት የውጭ ሀገራትን ጉዞ ሙሉ ለሙሉ አለማገዱን ገልጸው አላግባብ እየተካሄዱ ያሉ የውጭ ጉዞዎች ላይ እቀባ መጣሉን ጠቅሰዋል፡፡
ይሁንና የፊታችን ነሀሴ ወር ላይ የደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት ወይም ሳድክ ጉባኤን በዲሞክራቲክ ኮንጎ ተገኝተው እንደሚሳተፉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የማላዊ መገበያያ ክዋቻ የሚሰኝ ሲሆን ከዓለም አቀፍ የገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ድጋፍ ለማግኘት በማሰብ ከዶላር ጋር ያለውን ምንዛሬ በ25 በመቶ ዝቅ እንዲል አድርጋለች፡፡
በደቡባዊ የአፍሪካ ክፍል የምትገኘው ማላዊ 19 ሚሊዮን ህዝብ ብዛት ያላት ሲሆን ወደብ አልባ ሀገር ስትሆን ግብርና እና ቱሪዝም የኢኮኖሚዋ ዋነኛ መሰረቶች መሆናቸውን የዓለም ባንክ መረጃ ይጠቁማል፡፡