የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት በኮሮና ቫይረስ ተያዙ
በፕሬዝዳንቱ ላይ ቀለል ያሉ ምልክቶችን በማየታቸውንና ሕክምና እየተከታተሉ መሆኑን ጽ/ቤታቸው አስታውቋል
ራማፎዛ መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን ለምክትል ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማቡዛ በውክልና ሰጥተዋል
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ፕሬዝዳንት ራማፎዛ በኬፕ ታውን የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ደ ክለርክን መታሰቢያ ላይ ለመገኘት ከመታሰቢያ አገልግሎት ከወጡ በኋላ ጥሩ ስሜት እንዳልተሰማቸውም ተገልጾ ነበር።
ትናንትናም ባደረጉት ምርመራም ፕሬዝዳንት ራማፎዛ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ቀለል ያሉ ምልክቶችን በማየታቸው ሕክምና እየተከታተሉ ነው ተብሏል።
አሁን ላይ ፕሬዚዳንቱ ጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት የጤና አገልግሎት ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።
ፕሬዝዳንቱ ሙሉ በሙሉ መከተባቸው የተገለጸ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ በኬፕ ታውን ራሳቸውን አግልለው እንደሚገኙ ተገልጿል።
ራማፎዛ መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን ለቀጣይ ሳምንት ለሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማቡዛ በውክልና ሰጥተዋል ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳ እና ልዑካቸው ከሰሞኑ በአራት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ባደረጉት ጉብኝት በሁሉም ሀገራት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማድረጋውንም ጽህፈት ቤታቸው ጠቅሷል።
ፕሬዚዳንቱ እና የልዑካን ቡድናቸው ከሴኔጋል ሲመለሱ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ያደረጉ ሲሆን በምርመራውም ኮሮና እንዳልተገኘባቸውም ነው የተገለጸው።