ፕሬዚዳንት ራማፎሳ በደቡብ አፍሪካ ላይ እየተጣለ ባለው የጉዞ እገዳ “በጣም ተበሳጭቻለሁ” አሉ
በደቡብ አፍሪካ የተገኘውን አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ተከትሎ በርካታ ሀገራት የጉዞ ክልከላ እየጣሉ ነው
አሜሪካ፣ ብሪታኒያና የአውሮፓ ህብረት በደቡብ አፍሪካ ላይ የጉዞ ክልከላ ከጣሉ ሀገራት ውስጥ ናቸው
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ በሀገራቸው እና በጎረቤቶቻቸው ላይ እየተጣለ ያለው የጉዞ ክልከላ እንዳሳዘናቸው አስታወቁ።
ሀገራት እየጣሉት ባለው የጉዞ ክልከላ “በጣም ተበሳጭቻለሁ” ያሉት ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ፤ ውሳኔያቸው ምክንያታዊ ባለመሆኑ ክልከላውን በአስቸኳይ ሊያነሱ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
በደቡብ አፍሪካ ከሰሞኑ “ኦሚክሮን” የተባለ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መገኘቱ የሚታወስ ሲሆን፤ የዓለም ጤና ድርጅትም ዝርያውን “አሳሳቢ” ሲል መድቦታል።
ይህንን ተከትሎም በርካታ ዓለም ሀገራት ወደ ደቡብ አፍሪካም ይሁን ከደቡብ አፍሪካ ወደ ሀገራቸው ምንም አይነት በረራ እንዳይኖር የጉዞ ክልከላ በመጣል ላይ ይገኛል።
አሜሪካ፣ ብሪታኒያና የአውሮፓ ህብረት ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በቀጠናው ባሉ ሀገራት ላይ የጉዞ ክልከላ ከጣሉት ውስጥ ዋነኞቹ መሆናቸውም ተነግሯል።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ በሀገራቸው ላይ እየተጣለ ያለውን የጉዞ ክልከላ ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፤ “ፍትሃዊ ያልሆነ አድልዎ እየተፈፀመብን ነው” ብለዋል።
የጉዞ ክልከላዎች የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ጠቀሜታ የላቸውም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ እየተጣሉ ያሉ የጉዞ ክልከላዎች የሚያደርጉት አንድ ነገር በማገገም ላይ የነበረው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማዳከም ብቻ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በደቡብ አፍሪካ ላይ የጉዞ ክልከላ የጣሉ ሀገራት ውሳኔያቸውን በአስቸኳይ ሊሽሩ ይገባል ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በደቡብ አፍሪካ ላይ የጉዞ ክልከላ እየጣሉ ያሉ ሀገራት ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰበ ሲሆን፤ ሀገራቱ እየተከተሉት ያለው አካሄድም ሳይንሳዊ አይደለም ብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ማትሲዲሶ ማዎቲ፤ ኦሚክሮን የተባለው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በበርካታ የዓለም ሀገራት ላይ እየተገኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ አፍሪካን ብቻ ለይቶ የጉዞ ክልከላ መጣል ዓለም አቀፍ ትብብርን ይጎዳል ብለዋል።
የሀገሪቱ የጤና ሚኒስትር ጆ ፋህላ ባሳለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫም፤ በደቡብ አፍሪካም ሆነ በተወሰኑ የደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብ /ሳድክ/ አባል ሀገራት ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ እርምጃ “ሳይንሳዊ አይመስልም፤ የጉልበት እና የፍርሃት ምላሽ ነው” ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረትም ትናንት ባወጣው መረጃ፤ ‘ኦሚክሮን’ ከተባለው አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ጋር በተያያዘ ሃገራት ተቻኩለው የጉዞ እገዳዎችን መጣላቸውን ተቃውሟል።
በህብረቱ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግ የጉዞ እገዳዎች የቫይረሱን ስርጭት እንደማይገታ ከአሁን ቀደምም አይተናል ብለዋል።