‘ኦሚክሮን’ ቫይረስ በመላው ዓለም ከፍተኛ ስጋትን ደቅኗል- የዓለም ጤና ድርጅት
የጥንቃቄ መንግዶች እንዲተገበሩም ነው ድርጅቱ የጠየቀው
ድርጅቱ አባል ሃገራቱ የጀመሩትን የክትባት ዘመቻ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስቧል
‘ኦሚክሮን’ በሚል የሰየመው አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በመላው ዓለም ከፍ ያለ ስጋት መደቀኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡
ቫይረሱ በቀላሉ በመላው ዓለም ሊሰራጭ እንደሚችል ያስታወቀው ድርጅቱ የኮሮና ቫይረስ ከፍ ያለ ጉዳት ባደረሰባቸው አካባቢዎች የበለጠ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ገልጿል፡፡
194 አባል ሃገራቱ የጀመሩትን የክትባት ዘመቻ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የዓለም ጤና ድርጅት ያስታወቀው፡፡
የጥንቃቄ መንገዶች ተግባራዊ መደረጋቸውን እንዲከታተሉም አሳስቧል፡፡
አዲሱ ቫይረስ በደቡብ አፍሪካ ነው ተገኘ የተባለው፡፡ ከዚያም ወዲህ አንዳንድ ሃገራት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ማግኘታቸውን ሪፖርት አድርገዋል፡፡
ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ከጎረቤት ሃገራት በሚመጡ ተጓዦች ላይ እገዳዎች የጣሉ ሃገራትም ጥቂት አይደሉም፤ ምንም እንኳ የአፍሪካ ህብረት ጭምር እርምጃውን አጥብቀው ቢያወግዙም፡፡
በተያያዘ ዜና በስዊዘርላንድ ጄኔቭ ስብሰባ ላይ ያሉት የድርጅቱ አባል ሃገራት ለተጠናከረ የጋራ የወረርሽኝ ዝግጁነት ስምምነት አድርገዋል፡፡
በወረርሽኞች መከላከል፣ ዝግጁነት እና ትብብር ላይ አተኩሮ የሚሰራ በይነ መንግስታዊ ተቋም ለማቋቋምም ተስማምተዋል፡፡