"የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ኢኮኖሚ በሚያስደንቅ ሁኔታ ማደጉን ቀጥሏል" - ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ
ዩኤኢ ከነዳጅ ጥገኘነት የተላቀቀ ኢኮኖሚን ለመገንባት መስራት ከጀመረች ዋል አደር ማለቷ የሚታወቅ ነው
ፕሬዝዳንቱ ብዝሃነቱ የተጠበቀ ኢኮኖሚን ለመገንባት እንሰራለን ብለዋል
"የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ኢኮኖሚ በሚያስደንቅ ሁኔታ ማደጉን ቀጥሏል" ሲሉ ሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንት መሃመድ የዩኤኢን ቀጣይ የ10 ዓመታት እቅድ የተመለከተ ንግግርን ለሃገሪቱ ዜጎች እና ነዋሪዎች አድርገዋል፡፡
ሼክ መሃመድ በሞት የተለዩትን ወንድማቸውን ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያንን ተክተው የዩኤኢ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ያደረጉትና በቴሌቪዥን በቀጥታ የተላለፈ የመጀመሪያ ንግግራቸው ነው፡፡
በንግግራቸው የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት በማደግ ላይ ካሉና በጥንካሬያቸው ከሚጠቀሱ የዓለም ኢኮኖሚዎች መካከል ጠቅሰዋል፡፡
"ለፈጣሪ ምስጋና ይግባውና በተለያዩ ሃብቶች በዋናነትም በሰው ኃይል የታደልን ነን" ያሉት ሼክ መሃመድ ዩኤኢ እምቅ መስራት የሚችሉ ወጣቶች ሃብት እንዳላት ተናግረዋል፡፡
የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድ ከ200 የሚልቁ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች የጎላ አስተዋጽዖን በማበርከት ላይ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ፕሬዝዳንቱ ምጣኔ ሃብታዊ ብዝሃነትን ማስፈን ዋና የምጣኔ ሃብታዊው የግንባታ ሂደት መቃኛ መንገድ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን ለመገንባት በዘርፉ ርቀት መጓዝ የግድ ይለናልም ብለዋል፡፡
ብዙዎች በተራማጅነት የሚያወድሷቸው አዲሱ የዩኤኢ ፕሬዝዳንት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ ማን ናቸው?
ለዚህም የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አቅማችንን ማሳደግና መላቅ ይጠበቅብናልም ነው ሼክ መሃመድ ያሉት፡፡ ለዚህ የግሉ ዘርፍ ወሳኝ ሚናን ሊጫወት እንደሚችል በማስታወስም አበርክቶውን ለማሳደግ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ዩኤኢ ገና ከምስረታዋ አንስቶ ከሃገራት ጋር የቀረበ ወዳጅነትንና ትብብርን ለመመስረት መቻሏን አንስተዋል፡፡ በዚህም በዜጎቿ ጥረት በቀጣናዊም ሆነ በዓለም አቀፋዊ መድረኮች ክብርን መጎናጸፏን ነው የገለጹት፡፡
ይህን በመጪዎቹ ጊዜያትም ለማሳደግና በዓለም አቀፍ ደረጃ ልትጫወት የምትችለውን ሚና ጭምር ለማጠናከር እንሰራለን ብለዋል፡፡ የሰብዓዊ እና የበጎ አድራጎት ተግባራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ነው ሼክ መሃመድ የተናገሩት፡፡
ዩኤኢ በዓለም የኢነርጂ አቅርቦት ላይ የምትጫወተውን የቀዳሚነት ሚና ለማስቀጠል እንሰራለንም ብለዋል፡፡
አረብ ኤሚሬት ከነዳጅ ጥገኘነት የተላቀቀ አረንጓዴ ምጣኔ ሃብትን ለመገንባት መስራት ከጀመረች ዋል አደር ማለቷ ይታወሳል፡፡