ብዙዎች በተራማጅነት የሚያወድሷቸው አዲሱ የዩኤኢ ፕሬዝዳንት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ ማን ናቸው?
ሼክ መሀመድ የዩኤኢ የጦር ሃይሎችን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውም ይነገራል
ሼክ መሀመድ ለዩኤኢ እድገት ትልቅ አሻራ ካኖሩና በቅድሚያ ከሚጠቀሱ ተራማጅ መሪዎች አንዱ ናቸው
ሙሉ ስማቸው ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ይባላል፡፡ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) አዲሱ ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡
ሼክ መሃመድ ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን ወንድማቸውን ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያንን ተክተው ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 6 ቀን 2014 ዓ/ም የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡
ለለውጥ ባላቸው ቀናዒ አስተሳሰብና ተራማጅነታቸው የሚጠቀሱት ሼክ መሃመድ የዩኤኢ አካል በሆኑ ኤሚሬቶች ገዢዎች ጠቅላይ ምክር ቤት ተመርጠው ነው የዩኤኢ ፕሬዝዳንት የሆኑት፡፡
ለመሆኑ በተራማጅነት የሚጠቀሱት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ ማን ናቸው?
ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መስራች ፕሬዝዳንት ሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያን ሶስተኛ ልጅ ሲሆኑ የተወለዱትም በመጋቢት 11 ቀን 1961 አል ዐይን በተባለው የአቡ ዳቢ አካባቢ ነው።
ሼክ መሀመድ በሀገሪቱ ፈጣንንና ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ ትልቅ አሻራ ካኖሩና በቅድሚያ ከሚጠቀሱ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መሪዎች በቅድሚያ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በተለይም ዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኘው ሳንደኸርስት ሮያል ወታደራዊ አካዳሚ ከተመረቁበት ከፈረንጆቹ ከ1979 ጀምሮ የዩኤኢን ጦር ሃይል በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉና እንደፈረንጆቹ ጥር 2005 የሀገሪቱ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሆኖው እስከመሾም የደረሱ ታላቅ መሪ ናቸው፡
ሼክ መሀመድ በህዳር 2004 የአቡ ዳቢ ኤምሬትስ አልጋ ወራሽ ሆነው ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ ለአቡ ዳቢ እድገት ጉልህ አስተዋፅዖን አበርክተዋል፡፡ በርካታ የለውጥ እቅዶችን ነድፎ በመምራት ሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚ ያደረገ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ለውጥ እንዳመጡም ይነገርላቸዋል። ይህም ነው ለለውጥ ቀናዒ እና ተራማጅ ያሰኛቸው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን፤ አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን ጠንክረው በመታገል በዓለም ላይ የመቻቻል እና የሰላም ባህል እንዲስፋፋ ግንባር ቀደምና ታሪካዊ ተነሳሽነቶች ወስደው ስለመስራታቸው ይነገራል፡፡
ልዑሉ ከአረብ ኢምሬት ወታደራዊ ልሂቃን አንዱ ሲሆኑ እስከ አየር ኃይል አብራሪነትም ደርሰዋል፡፡ በበርካታ የኃላፊነት ቦታዎችም አገልግለዋል፡፡
በሀገሪቱ ጦር ከሚጫወቱት የመሪነት ሚና በዘለለ የአባታቸው የሼክ ዛይድ አል ናህያን የደህንነት ጉዳዮች አማካሪም ነበሩ፡፡
በአቡዳቢ ትምህርት እንዲስፋፋ፣ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ፣ ዩኤኢ ከነዳጅ ጥገኝነት የተላቀቀ ምጣኔ ሃብትን እንድትገነባ ለማድረግ የሚያስችል ወሳኝ የመሪነት ሚና ለመጫወት ስለመቻላቸውም ይነገራል፡፡