የተለያዩ ሃገራት መሪዎች ለሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ የእንኳን ደስ አለህ መግለጫ እየላኩ ነው
የአቡ ዳቢው ልዑል አልጋወራሽ የወንድማቸውን የሼክ ኸሊፋን ህልፈተ ህይወት ተከትሎ ነው በፕሬዝዳንትነት የተመረጡት
ሼክ መሃመድ የዩኤኢ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል
የተለያዩ ሃገራት መሪዎች ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ እየገለጹ ነው፡፡
መሪዎቹ የእንኳን ደስ አለህ መግለጫ በመላክም ላይ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወንድሜ ሲሉ የገለጿቸው ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ የዩኤኢ ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
የእንኳን ደስ አለህ የመልካም ምኞት መገልጫ መልዕክታቸውን በአረብኛ ያሰፈሩት ጠ/ሚ ዐቢይ በልዑሉ አመራር እድገትና ብልጽግና እንዲገኝም ተመኝተዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ሼክ መሃመድ ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
የኩዌት ኢምር እና ልዑል አልጋ ወራሽ፣ የኦማን ሱልጣን፣ የባህሬይን፣ የፍልስጤም፣ የሶሪያ መሪዎች እንዲሁም የኦስትሪያ ቻንሰለር እና የሌሎች ሃገራት መሪዎችም ለሼክ መሃመድ የእንኳን ደስ አለህ መልዕክትን ልከዋል፡፡
የዩኤኢ አካል የሆኑ ኤሚሬቶች ገዢዎች ምክር ቤት ነው ሼክ መሃመድ ወንድማቸውንና የአቡዳቢው ገዢ የነበሩትን ፕሬዝዳንት ሼክ ኸሊፋን ተክተው ዩኤኢን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ የመረጠው፡፡
በዱባዩ ገዥ፣ በዩኤኢ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሼክ መሃመድ ቢን ረሺድ አል መክቱም የሚመራው ምክር ቤቱ በአል መሽሪፍ ቤተ መንግስት ባደረገው ስብሰባ የሼክ መሃመድን ፕሬዝዳንትነት በሙሉ የድጋፍ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ትናንት አርብ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የዩኤኢ ፕሬዝዳንት እና የአቡ ዳቢ ገዢ የነበሩት የሼክ ኸሊፋ ስርዓተ ቀብር መፈጸሙ ይታወሳል፡፡