የዋግነር አመራሮችን ይዞ ስለተከሰከሰው አውሮፕላን እስካሁን የምናውቀው
ይቪግኒ ፕሪጎዥንን ጨምሮ ሰባት የዋግነር አመራሮችን ጭኖ ነበር የተባለው የግል ጄት ተከስክሶ ነው ወይስ ጥቃት ደርሶበት?
በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ እነማን ነበሩ? አሁን ምን እየተካሄደ ነው?
የሩሲያው ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን መሪው ይቪግኒ ፕሪጎዥን ህይወት ሳያልፍ አልቀረም የሚለው ዜና አሁንም የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት እንደሆነ ቀጥሏል።
የዋግነር ሌሎች አመራሮችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የግል ጄት ከሞስኮ በስተሰሜን ተከስክሶ ሁሉም ተጓዦች ህይወታቸው አልፏል።
በዚህ በረራ ተጓዥ ከነበሩት ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ የፕሪጎዥንም ተካቷል መባሉን ተከትሎ ነው የዋግነር መሪው ህይወቱ አልፏል የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ የሚገኙት።
ይሁን እንጂ ዋግነርም ሆነ የሩሲያ መንግስት ስለ ፕሪጎዥን ህልፈት በይፋ የተናገሩት ነገር የለም።
እስካሁን ስለተከሰከሰው አውሮፕላን የምናውቀው ምንድን ነው?
የሩሲያ አቪየሽን ባለስልጣን የዋግነር አመራሮችን የጫነው አውሮፕላን ከሞስኮ ወደ ሴንት ፒተርስበርግ እየበረረ እያለ ነው ትቬር በተባለ አካባቢ የተከሰከሰው።
ግሬይ ዞን በተባለውና ከዋግነር ጋር ግንኙነት ባለው ተቋም የቴሌግራም ገጽ ላይ የወጣው መረጃ ግን አውሮፕላኑ በሩሲያ ጦር ተመቶ መውደቁን ነው ያስታወቀው፤ ምንም እንኳን እስካሁን ማረጋገጫ ባያቀርብም።
ከወደ ሞስኮ በወጡ መረጃዎች በፕሪጎዥን የግል ጄት ሲጓዙ የነበሩት ሰባት ሰዎች እና ሶስት የበረራ ቡድን አባላት ሙሉ በሙሉ ህይወታቸው አልፏል።
አውሮፕላኑ 30 ደቂቃ እንኳን ሳይበር በእሳት ተያይዞ ስለመከስከሱ እየተነገረ ሲሆን፥ የተለያዩ አደጋውን የሚያሳዩ ምስሎችም እየወጡ ነው።
ሌላኛው የፕሪጎዥን የግል ጄት ግን በሞስኮ ክልል በሰላም ማረፉን የሚጠቅሰው ግሬይ ዞን ፕሮጎዥን በዚህኛው ጄት ውስጥ ስለመሆኑ ያለው ነገር የለም።
ተጓዦቹ እነማን ነበሩ?
የሩሲያ አቪየሽን ባለስልጣን በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ እየተጓዙ እንደሆነ ስማቸው የተዘረዘረው እነዚህ ናቸው ብሏል፦ ይቪግኒ ፕሪጎዥን፣ ዲሚትሪ ኡትኪን (የፕሪጎዥን ሁነኛ ሰው)፣ ሰርጌ ፕሮፑስቲን፣ ይቪግኒ ማካሪያን፣ አሌክሳንደር ቶትሚን፣ ቫለሪ ቼካሎቭ እና ኒኮላይ ማቱሴይቭ።
አብራሪው አሌክሲ ሌቭሺን፣ ረዳት አብራሪው ሩስታም ካሪሞቭ እና የበረራ አስተናጋጇ ክሪስቲና ራስፖፖቫ እንደሚሰኙም ባለስልጣኑ ገልጿል።
ፕሪጎዥን እና ፑቲን
የፑቲን ምግብ አብሳይ (ሼፍ) በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ይቪግኒ ፕሪጎዥን ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የረጅም ጊዜ ወዳጅነት አለው።
የዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድንን በመምራት በተለያዩ ሀገራት ግዳጁን የተወጣው ፕሪጎዥን በተለይ የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ስሙ እየገነነ መጥቷል።
የባክሙት ከተማን ለሩሲያ ጦር አስረክቦ ከወጣ በኋላ በሩሲያ ወታደራዊ አመራሮች ላይ ለአንድ ቀንም ቢሆን አመጽ መቀስቀሱ ግን ክሬምሊንን አስቆጥቶ ፑቲንንም ልባቸውን ሳያሻክር እንዳልቀረ ይገመታል።
አመጻው በቤላሩስ ፕሬዝዳንት አደራዳሪነት እንዲቆም ተደርጎ የሀገር ክህደት ክሱም የተነሳለት ፕሪጎዥን በቤላሩስ ቅጥረኛ ወታደሮችን ሲመለምል ቆይቷል።
የት እንደሚገኝ ሲያነጋግር ሰንብቶም ባለፈው ወር በፒተርስበርግ በተካሄደው የሩሲያ አፍሪካ ጉብኤ መታየቱ ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንትም “አፍሪካን ነጻ እያወጣን ነው” የሚልና በአፍሪካ መቀረጹን የሚገልጽ የቪዲዮ መልዕክት መልቀቁ አይዘነጋም።
በርግጥስ ይቪግኒ ፕሪጎዥን ህይወቱ አልፎ ከሆነ የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ ደርሶበት ነው ወይስ ጥቃት ተሰንዝሮበት የሚለው የሴራ ትንታኔ ቀጥሏል።
አሁን ምን እየተካሄደ ነው?
ሩሲያ የዋግነር አመራሮችን ጭኖ ሲጓዝ ተከሰከሰ ስለተባለው አውሮፕላን አደጋ የሚያታራ ልዩ ኮሚቴ አዋቅራለች።
አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ትቬር ግዛት አስተዳዳሪ ኢጎር ሩድንያም የምርመራ ሂደቱን በበላይነት እየመሩ ነው ተብሏል።
ከአደጋው የተረፈ ሰው ባለመኖሩም የአስቸኳይ ጊዜ የነፍስ አድን ስራው ቆሟል።