አፍሪካን ነጻ እያወጣን ነው - የዋግነር መሪ
የዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን መሪው ይቪግኒ ፕሪጎዥን በአፍሪካ ተቀርጿል የተባለ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፏል
ዋግነር በዩክሬን ከወጣ በኋላ ትኩረቱን አፍሪካ ላይ አድርጓል
የሩሲያው ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ዋግነር መሪው ይቪግኒ ፕሪጎዥን በአፍሪካ እንደሚገኝ የሚያመላክት ቪዲዮ ተለቋል።
በቡድኑ የቴሌግራም ገጽ በተለቀቀው ቪዲዮ ፕሪጎዥን መሳሪያ ታጥቆ ከኋላው በርቀት የሚጠብቁት ተዋጊዎች ተሽከርካሪ ውስጥ ሆነው ይታያሉ።
ሬውተርስ ግን ቪዲዮው የተቀረጸበትን ቦታም ሆነ ጊዜ ለይቶ ማወቅ እንዳልቻለ ገልጿል።
የዋግነር መሪው በዚሁ የቪዲዮ መልዕክቱ አፍሪካን ነጻ እያወጣናት ነው ሲል ተደምጧል።
“በዚህ ሙቀቱ ከ50 ዲግሪ በላይ ነው፤ ዋግነር ሩሲያን በአፍሪካ ብሎም በመላው አለም ተጽዕኖዋን እያሳደገ ይገኛል፤ አፍሪካውያን ፍትህ እንዲያገኙና ደስተኛ እንዲሆኑ እየታገልን ነው” ብሏል ፕሪጎዥን።
“የአይ ኤስ እና አልቃይዳ ክንፎችን ህይወት ቅዠት አድርገንባቸዋል” ሲልም በዚሁ የቪዲዮ መልዕክት ይደመጣል።
ቡድኑ አዳዲስ አባላትን እየመለመለ መሆኑን በመጥቀስም የተመዝገቡ ጥሪውን ማስተላለፉን ሬውተርስ ዘግቧል።
ዋግነር ከ2018 ጀምሮ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሊቢያ እና ማሊ ተልዕኮ ወስዶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ይታወሳል።
ቡድኑ በሀገራቱ መንግስታት ተጋብዞ ከገባ በኋላ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን የመንግስታቱ ድርጅት ይገልጻል።
ባለፈው ወር በፒተርስበርግ በተካሄደው የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት አማካሪ ጋር ሲጨባበጥ የታየው ይቪግኒ ፕሪጎዥን ትናንት ከአፍሪካ የተቀረጸ ነው የተባለ ቪዲዮ ለቋል።
አፍሪካን ነጻ እያወጣናት ነው ያለው መሪው የት ሆኖ ቪዲዪውን እንደቀረጸው እስካሁን አልታወቀም።
የዩክሬኗን ባክሙት ከተማ ለሩሲያ ጦር አስረክቦ የወጣው የዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን በአሁኑ ወቅት ዋና መቀመጫውን ቤላሩስ ማድረጉና የሀገሪቱን ወታደሮችም እያሰለጠነ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ቡድኑ ባለፈው ወር በዩክሬን ጦርነት እንደማይሳተፍና ቀጣይ ትኩረቱም አፍሪካ መሆኗን መግለጹ የሚታወስ ነው።