ጀነራል አብዱራህማን ትቺያኒ ራሳቸውን የኒጀር መሪ አድርገው ሾመዋል
የዋግነሩ አዛዥ ፕሪጎዥን የኒጀርን መፈንቅለ መንግሥት አወደሱ።
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ኒጀር ከሰሞኑ መፈንቅለ መንግሥት መፈጸሙ ይታወሳብ።
መፈንቅለ መንግሥቱ በፕሬዝዳንት መሀመድ ባዙም ጠባቂዎች የተፈጸመ ሲሆን ቆይቶም የሀገሪቱ ጦር ለመፈንቅለ መንግሥቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
በዩራኒየም ማዕድን ሀብቷ የምትታወቀው ኒጀር ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት 1960 ጀምሮ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ያለባት ሀገር ነበረች።
ጀነራል አብዱራህማን ትቺያኒ የኒጀር መሪ መሆናቸውን በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው አውጀዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ዋግነር አዛዥ የሆኑት የቨግኒ ፕሪጎዚን የኒጀትን ወታደሮች አድንቀዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
የቨግኒ በድምጽ ባሰራጨው መግለጫ "የኒጀር ወታደሮች ያደረጉት ነገር ህዝብ በቅኝ ገዢዎች ላይ እያደረጉት ያለን ትግል ማገዝ ነው" ብለዋል።
ኒጀር ፈረንሳይን ጨምሮ የአውሮፓዊያን ዋነኛ አጋር ተደርጋ የምትወሰድ ሀገር የነበረች ሲሆን መፈንቅለ መንግሥት ለተፈጸመባቸው ፕሬዝዳንት ባዙም ድጋፋቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
የኒጀር መፈንቅለ መንግሥት በበርካታ ሀገራት እና ተቋማት የተወገዘ ሲሆን አፍሪካ ሕብረት፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ እና አሜሪካ መፈንቅለ መንግስቱን አውግዘዋል።
በድህነቷ በዓለም የምትታወቀው ኒጀር የተትረፈረፈ የዩራኒየም ማዕድን ሀብት ቢኖራትም ህዝቦቿ በድህነት ውስጥ እንደሆኑ ይገልጻል።
በምዕራብ አፍሪካ መፈንቅለ መንግሥት እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ጊኒ በቅርቡ ሙፈንቅለ መንግስት የተፈጸመባቸው ሀገራት ናቸው።