“አሁን የፈተነን ኃይል ዳግመኛ የኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ እንዳይመጣ የሚያስችል ዘላቂ መፍትሔ ልንሰጠው ይገባል” ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመጀመሪያውን ምእራፍ አጠናቀው ለተወሰኑ ጊዜያት ወደ ቢሮ መመለሳቸውን አስታውቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው እለት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባወጡት መግለጫ፤ “ከጥቂት ጊዜያት በፊት ኢትዮጵያን ሊወጋ የተነሳውን ጠላት በጋራ ሆነን እንድንመክት ጦር ግንባር ላይ የያዝነው ቀጠሮ ጠላትን አንገት ሲያስደፋ ኢትዮጵያን ቀና አድርጓታል” ብለዋል።
በጦር ግንባር እየተከፈለ ያለው መስዕዋትነት የኢትዮጵያን የአሸናፊነት ስም የሚመልስ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ያቀረቡትን ጥሪ ተቀብለው ሕይወታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ሀብታቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ሞያቸውን ለሰጡ ሁሉ በኢትዮጵያ ስም አመስግነዋል።
- “ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ”- ጠ/ሚ ዐቢይ
- በአንድ ቀን ውጊያ ብዙ ድል ተግኝቷል፤ ድሉ ነገም ይቀጥላል- ጠ/ሚ ዐቢይ
“በዚሁ አጋጣሚ፣ የመጀመሪያውን ምእራፍ አጠናቅቄ ለተወሰኑ ጊዜያት ወደ ቢሮ መመለሴን እየገለጽኩ፣ ዛሬም ሆነ ወደፊት ጠላቶቻችን ጉልበታቸው ዝሎ፣ የጥላቻና የጠበኝነትን መንገድ ጥለው፣ የፍቅርና የሰላምን መንገድ እስኪመርጡ ትግላችን ይቀጥላል” ሲሉም አስታውቀዋል።
“ወደ ትግል የገባነው ሐቅን ይዘን ነውና የኢትዮጵያ አምላክ እንደ ወትሮው ከእኛ ጋር ነበር” ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ፤ ውድቀታችንን ሲመኙ የነበሩትን ሁሉ አሳፍሮ ዳግም የኢትዮጵያን ስም በወርቅ ቀለም እንድንጽፍ አስችሎናል” ብለዋል።
የመጀመሪያውን ምዕራፍ፣ “ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነትን” በሁለት ሣምንት ውስጥ መሳካቱን ያስታወቁ ሲሆን፤ የመከላከያ ሠራዊት፣ የየክልሎቹ ልዩ ኃይሎች፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላት እና የየአካባቢዎቹ ሚሊሻዎችና ታጣቂዎች በከፈሉት መሥዋዕትነት “ለልጆቻችን የምንነግረው ድንቅ ታሪክ ተሰርቷል” ብለዋል።
“ትግሉ ገና አልተጠናቀቀም፤ ነጻ ያልወጡ አካባቢዎች አሉን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ “አሁን የፈተነን ኃይል ዳግመኛ የኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ እንዳይመጣ የሚያስችል ዘላቂ መፍትሔ ልንሰጠው ይገባል” ሲሉም አስታውቀዋል።
“ላለፈው የምናመሰግንበት እንጂ ጨርሰናል ብለን እፎይ የምንልበት ወቅት ላይ አይደለንም፤ የተበተነው ጠላት እንዲማረክ ማድረግ አለብን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አካባቢያችንን ከበፊቱ በበለጠ ነቅተን የመጠበቂያ ጊዜው አሁን ነው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የፈረሰውን መልሰን መገንባት፣ የተፈናቀሉትን መመለስ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎቻችንንም ከበፊቱ በበለጠና በፈጠነ መንገድ ማሳለጥ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል።
ለሠራዊቱ የሚሰጠው ሁለንተናዊ ድጋፍ በዓይነትም በብዛትም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉ ሲሆን፤ “ያልዘመቱ ወገኖች ግማሽ ያህል ጊዜና ጉልበታቸውን ለዘማች ቤተሰቦች መስጠት ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።
ትግሉ በጦር ግንባር ብቻ አይደለም፤ በዲፕሎማሲውና በፖለቲካው ዘርፍ የምንሠራቸውን ሥራዎች በአዳዲስ መንገዶች እያከናወንን መቀጠል ይገባል ያሉ ሲሆን፤ “ወጭ ቆጥበን፣ ጊዜና ጉልበት ጨምረን፣ ለሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መሥራት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሁለት ሳምንት በፊት መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት መዝመታቸው ይታወሳል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር ከዘመቱ በኋላ የህወሓት ሃይሎች ይዘዋቸው የነበሩትን በርካታ የመንግስት ሃይሎች ማስለቀቅ ችለዋል።