ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ ከጦር ግንባር ሆነው መግለጫ ሰጥተዋል
ካሳ ጊታ ነፃ መውጣቱን እና ጭፍራ እና ቡርቃ ደግሞ ዛሬ ነፃ እንደሚወጡ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።
የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህምድ በዛሬው እለት ከጦር ግንባር ሆነው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ካሳ ጊታን ነፃ መውጣቷ ያስታወቁ ሲሆን፤ “ጭፍራን እና ቡርቃን ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎችን ዛሬ ነፃ እናስወጣለን” ብለዋል።
“የኢትዮጵያ ነፃነት እስኪረጋገጥ ወደኋላ አንልም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህምድ፤ “እኛ ምንፈልገው እኛ ሞተን የምትቆም ኢትዮጵያን ነው” ብለዋል።
“የጀመርነውን በድል እንደምናሳካ እርግጠኞች ነን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለዚህም ህዝባችን ከጎናችን ነው፤ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ምሁራንም ያቅማቸውን እየተወጡ ነው” ብለዋል።
“የእኔ ስራ ደግሞ በግንባር ሆኖ ጦርነቱንን እየመራሁ ድል ማምጣት ነው፤ በአንድ ቀን ውጊያ ብዙ ድል ተግኝቷል፤ ነገም ይቀጥላል በጣም ትላልቅ ድሎች አሉ” ሲሉም ተናግረዋል።
“ጠላት ከእኛ ጋር ሊፎካከር የሚችል አቅም የለውም፤ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣይ ትውልድ እናስተላለፍፋለን” ሲሉም ተናግረዋል።
የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሀምድ ባሳለፍነው ሰኞ፤ “ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ” ማለታቸው ይታወሳል።
“ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ” ሲሉም ጥሪ አቅርበው ነበረ።
የኢትዮጵያ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በሳለፍነው ረቡዕ ባወጣው መግለጫው፤ ድሎች እየተመዘገቡ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል።
በመግለጫውም በባቲ ግንባር በተደረገ ልዩ ኦፕሬሽን የህወሓት 6 የአርሚ እና የኮር ከፍተኛ መራሮች ተደምስሰዋል ያለ ሲሆን፤ በከሚሴ ግንባርም ህወሓትን ጦር ሲመሩ የነበሩ 6 ከፍተኛ የጦር አመራሮች ከነጠባቂዎቻቸው ተደምስሰዋል ብሏል።