ለህወሓት የተሰለፉ ሁሉ እጃቸውን እንዲሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥሪ አቀረቡ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሠራዊቱ በከፍተኛ ሞራል ላይ እንደሚገኝና ጠላትም እየተሸነፈ እንደሆነ ገልጸዋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእጅ ስጡ ጥሪውን ያስተላለፉት በአንደኛው የጦር ግንባር ነው ተብሏል
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር የተሰለፉ ሁሉ እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ አቀረቡ።
ውጊያ በመካሄድ ላይ ካለባቸው የጦር ግንባሮች በአንደኛው ተገኝተው በውጊያው የመጨረሻ ዕቅድ ላይ የመከሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአጠረ ጊዜና በአነስተኛ መሥዋዕትነት የኢትዮጵያ ድል የሚረጋገጥበትን መመሪያ መስጠታቸውን የመንግስት ብዙሃን መገናኛዎች በሰበር ዜና ዘግበዋል፡፡
ሠራዊቱ በከፍተኛ ሞራል ላይ እንደሚገኝና ጠላትም እየተሸነፈ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በተደናበረ ዕቅድ የገባው ጠላት ተደናብሮ መውጣት” እንደማይችል መናገራቸው ተገልጿል።
“ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ”- ጠ/ሚ ዐቢይ
ለህወሓት ዓላማ የተሰለፉ ሁሉ እጃቸውን በመስጠት ራሳቸውን እንዲያተርፉ፤ የትግራይ ወላጆችም ልጆቻችን የት ደረሱ ብለው እንዲጠይቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የኢትዮጵያ ፍላጎት ሰላምና ልማት ነው፤ ወደዚህ ጦርነት የገባነው ተገድደን ነው፤ ማሸነፋችን ግን አይቀሬ ነው” ሲሉ መናገራቸውም ነው የተገለጸው።
ዶ/ር ዐቢይ ከዚህ በፊት የህወሃት ታዋጊዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡