የኖርዌይ ጠ/ሚኒስትር የኮሮና ቫይረስ ገደቦችን በመጣስ ተቀጡ
በልደት በዓላቸው ላይ ከተፈቀደው ሰው በላይ በመገኘቱ የተቀጡት ጠ/ሚኒስትሯ ይቅርታ ጠይቀዋል
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ለፈጸሙት ጥሰት 2,300 ዶላር መቀጣቻውን ፖሊስ አስታውቋል
የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልበርግ የተቀጡት ፣ 60ኛ ዓመታቸውን ሲያከብሩ የተጋነነ የእራት ዝግጅት ባዘጋጁበት ወቅት ፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በሀገሪቱ የተጣሉትን እገዳዎች በመጣሳቸው እንደሆነም ነው ፖሊስ ያስታወቀው፡፡
ፖሊስ በልደት ዝግጅቱ የታደሙት እንግዶች ቁጥር ህጉ ከሚፈቅደው በላይ መሆኑንም ገልጿል፡፡
ልደታቸውን በማስመልከት ዬይሎ በተባለች ከተማ በሚገኝ አንድ ሬስቶራንት በተዘጋጀ የእራት ዝግጅት ላይ 13 የቤተሰቦቿ አባላት ተሰብስበው ማዕድ የተቋደሱ ሲሆን ፣ ይህም የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቀመጠውን የ10 ሰዎች ገደብ የጣሰ በመሆኑ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሯ የተቀጡት፡፡
በዚህ መሰረትም ጠቅላይ ሚኒስትሯ ለተፈጸመው ጥሰት 20,000 የኖርዌይ ክሮነር (2,300 ዶላር ገደማ) መቀጣቻውን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
“ሕግ ለሁሉም ሰው እኩል ከመሆኑ ባለፈ ፣ በጤና ህጎች ላይ የህዝብ አመኔታን ጠብቆ ለማቆየት የጠቅላይ ሚኒስትሯ መቀጣት ተገቢነ ነው” ሲሉ የፖሊስ ኮሚሽነሩ ኦሌ ሳቨርድ ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳን ጠ/ሚኒስትር ሶልበርግ እራት በተበላበት ሰዓት በስፍራው እንዳልነበሩ ቢገለጽም ፣ ፖሊስ ግን ዝግጅቱ እርሳቸው ያሰናዱት በመሆኑ ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ብሏል፡፡
ጠ/ሚኒስትሯ ለተፈጠረው ክስተት ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሯ “እኔ የበለጠ ጠንቃቃ መሆን ነበረብኝ ፤ እንደ እኔ ያለ ሰው ፣ ለዚያውም በየቀኑ ራስን ስለ መጠበቅ ሌሎችን የሚናገር ሰው፣ ደንቦቹን በተሻለ ማወቅ እና መተግበር ነበረበት” ሲሉ ቲቪ 2 (TV2) ለተባለ የሀገሪቱ ሚድያ ተናግረዋል፡፡
በኖርዌይ እስካሁን ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና የተያዙ ሲሆን 684 ሰዎች በቫይረሱ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡