የጋዛውን ጦርነት የሚቃወሙ ሰልፈኞች ኃይት ሀውስ ዙርያ ሰላማዊ ሰልፍ እያደረጉ ነው
በሰላማዊ ሰልፍ አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል
የተቃውሞ ሰልፉ በሚደረግበት የነጩ ቤት መንግስት አቅራቢያ እና በዋሽንግተን ዲሲ ጥበቃው ተጠናክሯል
ለ8 ወራት የዘለቀውን የጋዛ ጦርነት እንዲቆም በአሜሪካ በነጩ ቤተ መንግስት ዙርያ የተቃውሞ ሰልፍ እየተከናወነ ነው፡፡
እስራኤል በጋዛ የምታደርገው ፍትሀዊ ያልሆነ ጦርነት ከዚህ በላይ እንዲቀጥል መፈቀድ የለበትም ያሉት ሰልፈኞቹ አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም ጠይቀዋል፡፡
ኮድ ፒንክ እና የአሜሪካ እስላማዊ ህብረት ካውንስል ያዘጋጁት የተቃውሞ ሰልፍ ከዚህ ቀደም በባቡር ጣብያዎች፣ በአውሮፕላን ማረፍያዎች እና በተለያዩ ዩኒቨርስቲ ካምፓሶች አካባቢ ሲደርገ ቆይቷል፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ያቀኑት ሰልፈኞች ጦርነቱ እያደረሰ ያለውን ሰብአዊ ጉዳት የሚያሳዩ መፈክሮችን እና ፎቶዎችን ይዘው ታይተዋል፡፡
በተጨማሪም ተቃዋሚዎቹ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆባይደን ለ2024ቱ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ በሚያደርጉባቸው ስፍራዎች በመገኝት የጦርነቱን መቆም ሲጠይቁ ሰንብተዋል፡፡
ከትላንት ጀምሮ በሳምንቱ ቀናት በዋሽንግተን ዲሲ ይደረጋል በተባለው የተቃውሞ ሰልፍ በርከታ ሰዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። ይህን ተከትሎ በነጩ ቤተመንግስት አቅራቢያ እና በዋና ከተማዋ የደህንነት ጥበቃው ተጠናክሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት በፈረንሳይ በይፋዊ የስራ ጉብኘት ላይ የሚገኙት ጆ ባይደን ሰለማዊ ተቋውሞችን እንደሚያበረታቱ ነገር ግን ሰልፎቹ ወደ አመጽ እና ብጥብጥ እንዳይቀየሩ ጥንቃቄ እንዲደረግ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በዩኒቨርስቲ አካባቢዎች በተደረጉ ሰልፎች ከፖሊስ ጋር በተፈጠሩ ግጭቶች በእስር ላይ የሚገኙ ተቃዋሚዎች አሉ፡፡ ከሳምንታት በፊት በካሊፎርኒያ እና ሎስአንጀለስ ዩኒቨርስቲዎች ሰልፈኞቹ ከጦርነቱ ደጋፊዎች ጋር በፈጠሩት እሰጣገባ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
ጦርነቱን ተከትሎ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ጸረ ሴማዊነት እና ጸረ ሙስሊም እንቅስቃሴዎች በማደግ ላይ እንደሚገኙ የአሜሪካ የሀገር ውስጥ የደህንነት ተቋማት ሪፖርቶችን አውጥተዋል፡፡
የኦክተበር 7ቱን የሀማስ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ የከፈተችውን ጦርነት ለማስቆም የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት እና ሀገራት ተጽእኖ እያሳደሩ ቢገኝም ጦርነቱን እስካሁን ሊገታው አልቻለም፡፡
አሜሪካ በሁለቱ አካለት በኩል ጊዜያዊ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም ወደ ውይይት እንዲመጡ የስምምነት ረቂቅ ማዘጋጀቷ ይታወሳል፡፡ በጦርነቱ በጋዛ እስካሁን ከ2.3 ሚልየን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ሲነገር 36ሺ ንጹሀን ደግሞ ህይወታቸው አልፏል፡፡
በእስራኤል በኩል 1200 ንጹሀን ሲገደሉ በአሁኑ ወቅት 80 የእስራኤል ዜግነት ያላቸው ሰዎች በሀማስ ታግተው ይገኛሉ፡፡