እስራኤል ባይደን ያቀረቡትን የተኩስ አቁም ስምምነት ሀሳብ እየመረራት መቀበሏን የኔታንያሁ አማካሪ ተናገሩ
እስራኤል ሀማስን ጨርሳ እስከምትደመስስ ድረስ ጊዜያዊ የሆነ ተኩስ አቁም ብቻ መፈለጓ ስምምነት ላይ እንዳይደረስ ካደረጉ ነጥቦች መካከል አንዱ ነው
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ባይደን ባቀረቡት የስምምነት ሀሳብ "ተስማምናል፤ ነገርግን ጥሩ የሚባል ስምምነት አይደለም" ተናግረዋል
እስራኤል ባይደን ያቀረቡትን የተኩስ አቁም ስምምነት ሀሳብ እየመረራት መቀበሏን የኔታንያሁ አማካሪ ተናገሩ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አማካሪ እስራኤል ባይደን ጦርነቱን ለማስቆም ያቀረቡት የተኩስ አቁም ስምምነት እቅድ የሚጎድሉት ነገሮች ቢኖሩም መቀበሏን አረጋግጠዋል።
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ የሆኑት ኦፊር ፋልክ ከእንግሊዙ ሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ባይደን ባቀረቡት የስምምነት ሀሳብ "ተስማምናል፤ ጥሩ የሚባል ስምምነት አይደለም። ነገርግን ሁሉም ታጋቾች እንዲለለቁ እንፈልጋለን" ሲሉ መናገራቸዉን ሮይርስ ዘግቧል።
"በርካታ ዝርዝር ነገሮች መሰራት አለባቸው" ያሉት አማካሪው የታጋቾችም መለቀቅን ጨምሮ እስራኤል ባቀረበቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች እና ዘርአጥፊ በሆነው ሀማስ መደምሰስ" ዙሪያ ያሏት አቋሞቿ እንዳልተቀየሩ ገልጸዋል።
ፕሬዝደንት ባይደን የኔታንያሁ መንግስት አቅርቦታል ያሉትን ሶስት ምዕራፍ ያለው የተኩስ አቁም እቅድ ባለፈው አርብ እለት ነበር ይፋ ያደረጉት።
የመጀመሪያው ዙር ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና የተወሰኑ ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚያስችል ሲሆን ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ላልተወሰነ ጊዜ ተኩስ አቁም ተደርጎ የቀሩት በህይወት ያሉ ታጋቾች እንዲለቀቁ እንደማደረግ ባይደን ተናግረዋል።
ባይደን ከዚህ ቀደም ባለፈው አርብ እለት ካቀረቡት ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው በርካታ የተኩስ አቁም የስምምነት ሀሳብ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ባይደን ባለፈው የካቲት ወር እስራኤል በረመዳን ፆም ሲጀምር ተግባራዊ የሚሆን ተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማማምታለች ብለው ነበር። ነገርግን ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ አልሆነም።
እስራኤል ሀማስን ጨርሳ እስከምትደመስስ ድረስ ጊዜያዊ የሆነ ተኩስ አቁም ብቻ መፈለጓ ስምምነት ላይ እንዳይደረስ ካደረጉ ነጥቦች መካከል አንዱ ነው።
ሀማስ በበኩሉ ታጋቾችን የሚለቀው ዘላቂ ተኩስ አቁም ተደርሶ ተኩስ ከቆመ ብቻ ነው ከሚለው አቋም ሸርተት ለማለት ፍላጎት አላሳየም።
ባይደን ባሰመት ንግግር የአሁኑ እቅዳቸው ሀማስ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ በጋዛ ጥሩ ጊዜ እንዲመጣ የሚያስችል ነው ብለዋል። ይህ እንዴት ሊከወን እንደሚችል ያላብራሩት ባይደን "ከመጀመሪያው ምዕራፍ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ለመሸጋገር በዝርዝሮች ላይ ድርድሮች ይኖራሉ" ብለዋል።
እስራኤል የሀማስ የመጨረሻ ምሽግ ይገኝባታል የምትላትን በግብጽ ድንበር የምትገኘውን የራፋ ከተማ ለመቆጣጠር እያደረገች ባለው እንቅስቃሴ የጋዛ-ግብጽ ድንበርን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሯን መግለጿ ይታወሳል።
ባለፈው ጥቅታ ወር ሀማስ በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ እስራኤል እያካሄደች ባለው ጥቃት ከ35ሺ በላይ ፍልስጤማውያን መገዳላቸው የጋዜ የጤና ባለስልጣናት ገልጸዋል።