እስራኤል ፍልስጤማውያን በተጠለሉበት ትምህርት ቤት የሚሳኤል ጥቃት ፈጸመች
በኑሴራት የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ በሚገኘው ትምህርት ቤት በተፈጸመው ጥቃት 27 ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል
የእስራኤል ጦር በበኩሏ ትምህርት ቤቱ በጥቅምት 7ቱ ጥቃት የተሳተፉ የሃማስ ታጣቂዎች የመሸጉበት እንደነበር ነው ያስታወቀው
እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ተፈናቃዮች በተጠለሉበት የመንግስታቱ ድርጅት ትምህርት ቤት ላይ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 27 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።
የእስራኤል ጦር በኑሴራት የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ የሚገኘው ትምህርት ቤት በጥቅምት 7ቱ ጥቃት የተሳተፉ የሃማስ ታጣቂዎች ምሽግ እንደነበር አስታውቋል።
በአውሮፕላን በተፈጸመው ጥቃትም የቡድኑ ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን ነው የጠቆመው።
ሃማስ የሚያስተዳድረው የጋዛ ሚዲያ ተቋም ዳይሬክተሩ ኢስማኤል ኣአል ታዋብታ በበኩላቸው በማዕከላዊ ጋዛ የሚገኘው የኑሴራት ካምፕ ትምህርት ቤት የሃማስ ማዘዣ ጣቢያ ሆኗል በሚል በእስራኤል የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርገዋል።
“ወራሪው ሃይል የተቀነባበሩ ሀሰተኛ ታሪኮችን በመፍጠር ህዝቡን ማደናገርና በተፈናቀሉ ወገኖቻችን ላይ ለሚፈጽሙት አሰቃቂ ወንጀል ምክንያት መደርደራቸውን ቀጥለዋል” ሲሉም ዳይሬክተሩ ለሬውተርስ ተናግረዋል።
የእስራኤል ጦር ግን የእስራኤል ጄቶች ጥቃቱን ከመፈጸማቸው በፊት የንጹሃንን ጉዳት ለመቀነስ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው ያስታወቀው።
ስምንተኛ ወሩን የያዘው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት አሁን ላይ ዋነኛ ትኩረቱን ራፋህ ላይ ቢያደርግም እስራኤል በማዕከላዊ ጋዛም ፈጣን ጥቃት ፈጽመው የመሰወር ታክቲክ ይከተላሉ ባለቻቸው የሃማስ ታጣቂዎች ላይ የአየር ጥቃት ማድረሷን ቀጥላለች።
ከ36 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው ጦርነት እስከ 2024 መጨረሻ ሊዘልቅ ይችላል የሚል አስተያየትን የሚሰጡ የእስራኤል ባለስልጣናት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረጉ መሆኑ ይነገራል።
የጥምር መንግስቱን የመሰረቱ ፓርቲዎች መሪዎችም ኔታንያሁ በቅርቡ በአሜሪካ የቀረበውን የተኩስ አቁም እቅድ ከተቀበሉ ስልጣን ለቀው የጥምር መንግስቱን እንደሚያፈርሱ ሲዝቱ ሰንብተዋል።
የሃማስ መሪው ኢስማኤል ሃኒየህ በበኩላቸው የባይደን የተኩስ አቁም እቅድ የእስራኤል ጦር ሙሉ በሙሉ ከጋዛ እንዲወጣና ጦርነቱ በዘላቂነት እንዲቆም የሚጠይቅ ሃሳብ ሊያካትት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአሜሪካው የስለላ ተቋም (ሲአይኤ) ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ በትናንትናው እለት በዶሃ ከኳታርና ግብጽ አደራዳሪዎች ጋር መምከራቸው ቢገለጽም በአጣማሪ ፓርቲዎቻቸው ጫናው ያየለባቸው ቤንያሚን ኔታንያሁ በቅርቡ ከሃማስ ጋር ተኩስ የማቆም ስምምነት ይደርሳሉ ተብሎ አይጠበቅም።