የመንግስት ዩንቨርሲቲዎች በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ከመንግስት ቁጥጥር ነጻ ሊሆኑ ነው
የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ከመንግስት ነጻ ሆኖ ራሱን ማስተዳደር ሊጀምር መሆኑን ተገለጸ
የመንግስት ዩንቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ነው
የመንግስት ዩንቨርሲቲዎች በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ከመንግስት ቁጥጥር ነጻ እንደሚሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ ሆኖ የመመራት መብት የሚሰጥበት የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲን ተከትሎ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ በሂደት ወደ ነጻ ዩኒቨርሰቲነት እንደሚቀየሩ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ውጪ በመሆን ነጻ ተቋም እንዲሆን የተወሰነውም መንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን በራስ ገዝ አስተዳደር እንዲተዳደሩ የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሳው ወልደሃና “የዩኒቨርሲቲዎች በነጻ የመመራት ፈተና እና እድል” በሚል የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡
በጽሑፋቸውም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ዩኒቨርሲቲዎች ነጻነታቸው ተጠብቆ የመምራት፣ ሰራተኛ የመቅጠር፣ተማሪን የመቀበል፣ ሃብት የማፍራትና የማስተዳደር፣ ከተቋማት ጋር በራስ ግንኙነትን በመፍጠር የሁለትዮሽ ስራን ማጠናከር፣ የራሳቸውን አቅም የሚፈቅደውን ደረጃዎችን ማውጣትና መሰል ተግባራትን መፈጸም እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ ባለመሆናቸው ምክንያት ይህን ሁሉ ማድረግ አይችሉም ያሉት ፕሮፌሰር ጣሳው፣በዚህ ምክንያትም የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በሚፈልጉት ፍጥነትና ጥራት ማከናወን አለመቻላቸውን ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች በራስ የሚተዳደሩ ነጻ ተቋም ሲሆኑም አቅማቸውንና ብቃታቸውን ያገናዘበ ውሳኔዎችን በመወሰን የተሻለና አገር የሚጠቅሙ ተግባራት እንደሚከናወኑ ፕሬዝዳንቱ መናገራቸውን ፋባ ብሮድካስቲንግ ዘግቧል።
ነጻ ዩኒቨርሲቲ እውቅናው በሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው ከዚህ ቀደም ባለው ልምድና የተሻለ አቅም ላይ የሚገኝ በመሆኑ ነው ተብሏል።
ነጻ ዩኒቨርሲቲ ማለት ከመንግስት ተመጣጣኝ በጀት የሚያገኝና ዩኒቨርሲቲዎች የተሰጣቸው የነጻነት ስፋትን በአአግባቡ መጠቀማቸውን የሚቆጣጠር ሆኖ ከዛ ውጪ አንድ የግል ተቋም ሊያደርገው የሚችለውን ተግባር በሃላፊነት የማድረግ መብት የሚሰጥ ነው።
ከዚህ ባለፈም ተማሪዎችን በራሱ ፈትኖ መቀበል፣ ስኮላር ሺፕ መስጠት፣ የወጪ መጋራትን በራሱ አካሄድ መተግበር የሚችል፣ መምህራንን በፈለገው ጊዜ የሚቀጥር፣ በአቅሙ የሚከፍልና እርምጃም የሚወስድ፣ የፋይናንስ አስተዳደርን በራሱ የሚመራ እና ሌሎችም ተግባራትን በነጻነት የመከወን መብት የሚሰጥ ነው ተብሏል።