የ8ኛ እና 12ኛ ከፍል ብሄራዊ ፈተናዎች በወርሃ ህዳር መጨረሻይሰጣሉ ተባለ
የአከፋፈት ሂደቱን በተመለከተ ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ውይይት እየተካሄደ ነው
ትምህርት ቤቶች ከመጪው ጥቅምት 9 ጀምሮ እንዲከፈቱም ምክረ ሃሳብ ቀርቧል
ትምህርት ቤቶች ከመጪው ጥቅምት 9 ጀምሮ ይከፈታሉ ተባለ
የትምህርት ቤቶች አከፋፈት ሂደት በሶስት ዙር እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡
በመጀመሪያው ዙር ማለትም ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ የውሳኔ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።
በ2ኛ ዙር ጥቅምት 16 ቀን 2013 ደግሞ በሁሉም የዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ ነው ምክረ ሃሳብ የቀረበው።
በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት እንዲጀምሩ የውሳኔ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።
ትምህርት ቤቶችን ዳግም መክፈት በሚቻልበት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት እየተካሄደ ነው።
በ ውይይቱ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ሚኒስትሮችም ተገኝተዋል።
ውይይቱ የ8ኛ እና 12ኛ ከፍል ብሄራዊ ፈተናና የግል ትምህርት ቤቶችን የትምህርት አሰጣጥ ሂደት እንዴት መሆን አለበት የሚለውንም ይመለከታል።
ባለፉት ሁለት ቀናት ከሁሉም ክልሎች የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በተካሄደ ውይይት የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን አስመልክቶ ሁሉም ተፈታኞች ለፈተና ይቀመጡ የሚል የውሳኔ ምክረ ሃሳብ መቅረቡን የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂነር) ገልጸዋል።
የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሕዳር 22 እና 23 ቀን 2013 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን ፈተና ላይ መቀመጥ የሚችሉት 7ኛ ክፍልን ተምረው ያጠናቀቁና የ8ኛ ክፍልን የአንደኛ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው።
በተመሳሳይ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መውሰድ የሚችሉት የ11ኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀቁና የ12ኛ ክፍልን የመጀመሪያ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው ተብሏል።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሕዳር 28 እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚሰጥም በምክረ ሀሳቡ ላይ ተጠቅሷል።
የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን በተመለከተ ለመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚወጣው መመዘኛ በግል ትምህርት ቤቶችም ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።
የግል ትምህርት ቤቶች የምዝገባ ክፍያ በ2012 ዓ.ም በነበረው መጠንና የክፍያ ስርዓት መሆን እንዳለበትም ተገልጿል።
የትምህርት ቤቶች የክፍያ ስርዓት በባንክ በኩል ብቻ መፈጸም እንዳለበትም ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።
በቀረበው ምክረ ሃሳብ ላይ የሚደረገው ውይይት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡