ፓፓኒው ጊኒ ወደ ውጭ ሀገራት ከምትልካቸው ምርቶች መካከል 40 በመቶ ያህሉ የዘይት ምርቶች ናቸው
ፓፓ ኒው ጊኒ የዘይት ሚንስትር ሾመች።
ዘጠኝ ሚሊዮን ገደማ ህዝብ ብዛት ያላት እስያዊቷ ሀገር ፓፑዋ ኒው ጊኒ የዘይት ሚኒስቴር ያቋቋመች ሲሆን ጉዳዩ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ከአንድ ወር በፊት በድጋሚ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው የተመረጡት ጄምስ ማራቢ አዲሱን ካቢኔያቸውን አዋቅረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 33 አባላት ባለው በአዲሱ ካቢኔያቸው የዘይት ሚኒስትር የሾሙ ሲሆን ሀገሪቱ ወደ ውጪ የምትልካቸውን መሰረታዊ የግብርና ምርቶች ለማሳደግ ማቀዷ ለአዲሱ ሚንስቴር መቋቋም ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።
ፓፑዋ ኒው ጊኒ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የምትታወቅ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የዘይት ምርቶች 40 በመቶ ድርሻ ሲኖራቸው ቡና ደግሞ የ27 ድርሻ አለው።
ወደ ውጪ ሀገራት የሚላከውን የዘይት ምርት ለማሳደግ ሲባልም ሚንስቴር ተቋም ለማቋቋም መወሰኗን ጠቅላይ ሚንስትር ማራፒ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲሱ ካቢኔያቸው ከዘይት ሚንስትር በተጨማሪ የቡና ሚንስትር የሾሙ ሲሆን የተቋሙን ዋና መቀመጫ ከዋና ከተማው ወደ ገጠር አዛውረዋል።
ጆ ኮሊ የፓፑዋ ኒው ጊኒ የቡና ሚንስትር ተደርገው የተሾሙ ሲሆን የሚንስቴሩ ዋና መቀመጫ ጽህፈት ቤት ቡና በብዛት ወደሚመረትበት ደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል ይሆናል ተብሏል።