መንግስት የተመረጡ የህወሓት ወታደራዊ ዐቅሞችን እንደሚመታ አስታወቀ
በወታደራዊ መሣሪያዎችና ማሠልጠኛዎች አቅራቢያ ያሉ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ራሳቸውን እንዲያርቁ አሳስቧል
የህወሓት ቡድን አሁንም ጥቃት መሰንዘሩን መቀጠሉንም ነው የገለጸው
መንግስት "የተመረጡ የህወሓትን ወታደራዊ ዐቅሞች" እንደሚመታ አስታወቀ፡፡
“እስካሁን ድረስ በሬን ለሰላም ክፍት በማድረግ ስጠባበቅ ነበር” ያለው መንግስት "ህወሓት ጥቃቱን ቀጥሎበታል" ብሏል።
በመሆኑም ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር የገለጸው ዝግጁነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ "ለህወሓት ፀረ ሰላም ዕብሪት ምንጭ የሆኑ ወታደራዊ ዐቅሞችን ዒላማ ያደረገ ርምጃ ይወስዳል" ሲል እርምጃውን የተመለከተ አስቸኳይ መልእክት በኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ በኩል አውጥቷል፡፡
በመግለጫው በወታደራዊ መሣሪያዎች እና ማሠልጠኛዎች አቅራቢያ ያሉ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ራሳቸውን እንዲያርቁም አሳስቧል።
ቀደም ሲልም "ሰላማዊ መንገድ እንዳይዘጋ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሕወሓትን ወደ ሰላም መንገድ ሊያመጣው ይገባል" ሲል መግለጫ አውጥቶ የነበረው ኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ "ያለ ጦርነት መኖር የማይችለው ህወሓት ለሰላም የተከፈቱትን በሮች ሁሉ እየዘጋቸው ነው።
የመከላከያ ኃይላችን ይዞ በቆየባቸው ቦታዎች ላይ አሁንም ጥቃት እየፈጸመ ይገኛል። የመከላከያ ኃይላችን የመንግሥትን የሰላም አማራጭ በመያዝ በጥንቃቄ በመከላከል ላይ ነው" ሲል ገልጿል።
እስካሁን በመንግሥት በኩል የተደረጉ የሰላም ጥረቶችና የከፈላቸው ዋጋዎች ይታወቃሉ ያለው አገልግሎቱ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በማሰብ የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉን፣ ለእርዳታ የሚገቡ መኪኖችና ቁሳቁሶች ላልተገባ ተግባር መዋላቸውን እያወቀ እንኳን፣ ለሕዝቡ ሲባል፣ ወደ ክልሉ ሰብአዊ ርዳታ ያለ ችግር እንዲገባ ሁሉንም ነገር ማመቻቸቱን አስታውሷል።
የድርድር ዕቅዱንና ተደራዳሪዎቹን ይፋ በማድረግ በማናቸውም ጊዜ፣ ቦታ እና ጉዳዮች ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን ማሳወቁምንም ነው የገለጸው፡፡
በመሆኑም፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ "አሁን በግልጽ እንደታየው ሕወሐት ነዳጅ ዘራፊ ብቻ ሳይሆን ጠብ ጫሪ መሆኑን ዐውቆ ማውገዝ አለበት" ብሏል፡፡
"ሁለቱ ወገኖች" ከሚል ፍርደ ገምድል ጥሪ ተላቆ ሕወሐት፤ መንግሥት ወደ ያዘው የሰላም አማራጭ እንዲመጣ ግፊት ያድርግ ሲልም ጥሪ አድርጓል፡፡
ይህ ካልሆነና ሕወሐት ጥቃቱን የሚቀጥል ከሆነ፣ መንግሥት በሕግ የተጣለበትን ግዴታ ለመወጣት ሲል ማንኛውንም ርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ ይሆናል ሲል አሳውቋል።