በኢትዮጵያ የተጀመረው የአቮካዶ ዘይት ምርት ለአርሶአደሩ ብሩህ ተስፋ ፈንጥቋል
ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የአቮካዶ ዘይት ለዉጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል
በኢትዮጵያ ከሚገነቡ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፓርኮች አንዱ የሆነው የይርጋለም ፓርክ ኢንቨስተሮችን በማስተናገድ ላይ ነው
በኢትዮጵያ የተጀመረው የአቮካዶ ዘይት ምርት ለአርሶአደሩ ብሩህ ተስፋ ፈንጥቋል
ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በኢትዮጵያ በግንባታ ላይ ከሚገኙ አራት መሰል ፓርኮች አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ፓርኮች የግብርና ዉጤቶችን ብቻ አቀነባብረው ለሀገርዉስጥ እና ለውጭ ተጠቃሚዎች ለማቅረብ ታልመው የሚገነቡ ናቸው፡፡ በዚህም በዋናነት ግብርናውን በማዘመን እና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶአደሩን ህይወት መቀየር እንዲሁም ለወጣቱ የስራ እድል መፍጠር የፓርኮቹ ተልዕኮ መሆኑን ነው መንግስት የሚገልጸው፡፡
በሲዳማ ክልል የሚገኘው የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በአሁኑ ወቅት የዉሃ ፣ የመብራት ፣ የመንገድ ፣ የአገልግሎት ሰጪ ህንጻዎችን እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በመጀመሪያ የግንባታ ምዕራፉ አጠናቆ ኢንቨስተሮችን ማስተናገድ ጀምሯል፡፡
የደቡብ ክልል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብሩ ወልዴ ለአል ዐይን እንደገለጹት 152 ፋብሪካዎችን የመያዝ አቅም ባለው በፓርኩ በአሁኑ ወቅት 11 የፋብሪካ ሼዶች የተገነቡ ሲሆን ከነዚህም 4 ሼዶች የፋብሪካ ተከላ እና ሌሎች ዝግጅቶችን አጠናቀው ምርት ማምረት ጀምረዋል፡፡ ሌሎች በርካታ ባለሀብቶችም በፓርኩ ኢንቨስት ለማድረግ በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡
አቶ ብሩ ወልዴ
ምርት ከጀመሩ አራት ፋበሪካዎች መካከል አንዱ ‘ሳንቫዶ’ የተሰኘ የኔዘርላንድስ (ሆላንድ) የአቮካዶ ዘይት አምራች ኩባንያ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ፋብሪካው እስካሁን ለ6 ዙር የአቮካዶ ዘይት ለዉጭ ገበያ አቅርቧል፡፡
ኩባንያው ከፓርኩ ጋር በመሆን የአቮካዶ ግብአት አቅርቦት ላይ በተጓዳኝ እየሰራ እንደሚገኝም ስራ አስፈጻሚው አብራርተዋል፡፡
ኩባንያው በፓርኩ 40 ኪ.ሜ ሬዲየስ ላይ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን ቀጥሮ በራሱ የሞባይል መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) እየተከታተለ ከአርሶአደሩ ጋር መስራት ጀምሯል፡፡ በዚህም 73 ሺ አርሶአደሮችን አቅፏል፡፡ 80 ምርት መሰብሰቢያ ማዕከላት አሉት፡፡ ከአርሶአደሩ የአቮካዶ ምርቱን እየመዘኑ የሚገዙ የህብረት ስራ ማህበራትም አብረውት ይሰራሉ፡፡ በዚህ የተሳሰረ ሰንሰለት የሚሰሩት ማህበራቱ በአንድ ኪ.ግ 1 ብር ያገኛሉ፡፡ በቀን እስከ 52 ቶን አቮካዶ ለፋብሪካው ይቀርባል፡፡
በሶስት ፈረቃ ስራውን የሚያከናውነው ፋብሪካው፣ በዓመት ለ9 ወራት ያለምንም መቆራረጥ ይሰራል፡፡
አርሶአደሩ በፊት ለቤት ፍጆታ አሊያም ለአካባቢ ገበያ ብቻ ያቀርብ የነበረውን የአቮካዶ ምርት አሁን በአካባቢው የሚረከበው ፋብሪካ በማግኘቱ ተጠቃሚነቱ እንደጨመረ መሆኑንአቶ ብሩ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም አርሶአደሩ አሁን ምርቱን ለማሳደግ በመጣጣር ላይ ነው፡፡
በሲዳማ ክልል በአቮካዶ ምርት ላይ የተጀመረው እንቅስቃሴ “የኢትዮጵያ ግብርና እየዘመነ ስለመሆኑ ማሳያ ነው” ይላሉ አቶ ብሩ ወልዴ፡፡ ከዚህ ቀደም “አንድ የአቮካዶ ችግኝ ፍሬ ለመስጠት 7 ዓመት ይፈጅበት ነበር” ያሉት አቶ ብሩ አሁን “የተሸሻሉ ዝርያዎችን በማልማት ከ3 ዓመት በታች ፍሬ መሰብሰብ ተችሏል” ብለዋል፡፡ የተሻሻሉ ዝርያዎች እንደየአካባቢው ሁኔታ ከ 8 ወር እስከ 3 ዓመት ፍሬ ይሰጣሉ፡፡ 1 ዛፍ በዓመት 2 ጊዜ ምርት ይሰጣል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሳንቫዶ ኩባንያ ተጽእኖው የጎላ እንደሆነም አቶ ብሩ ከአል ዐይን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
አቮካዶን ጨምሮ ለፓርኩ ኢንዱስትሪዎች ግብአት የሚሆኑ ፓፓያና ሌሎች ፍራፍሬዎችም ከአርሶአደሩ አነስተኛ ማሳዎች በተጨማሪ በሰፋፊ እርሻዎችም እየለሙ ይገኛሉ፡፡
አቮካዶ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በብዛት ቢመረትም “በኢትዮጵያ የሚመረተው ኦርጋኒክ መሆኑ ለየት ያደርገዋል” ያሉት አቶ ብሩ “የጣለሊያን ባለሙያዎች በኢትዮጵያ አቮካዶ ላይ ምርምር አድርገው ተወዳዳሪ እንደሌለው መስክረዋል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የአቮካዶ ዘይት ለምግብነት እና ለመዋቢያ ኢንዱስትሪዎች ይውላል፡፡ ፍሬው ደግሞ ለጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ‘ለስታርች’ ምርት ፣ ለፊት ‘ስክራፕ’ እና ለሌሎችም ምርቶች ያገለግላል፡፡ በመሆኑም በዘርፉ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የገለጹት አቶ ብሩ ይህም ለአርሶአደሩ ትልቅ እድል መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
ወደ ፓርኩ ለሚመጡ ኢንቨስተሮች ሼድ በሁለት መንገድ የሚሰራ ሲሆን አንዱ በኢንቨስተሮቹ ፍላጎት በመንግስት የሚሰራ ነው፡፡ ይህም በ30 ዓመት ኪራይ ይቀርብላቸዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኢንቨስተሮች ራሳቸው መስራት ከፈለጉ በፈለጉት መጠን መሬት ይዘጋጅላቸውና ለ70 ዓመት እንደሚከራዩ አቶ ብሩ ገልጸዋል፡፡ በፓርኩ ቅጥር ጊቢ ባንክን ጨምሮ ሁሉም አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል አገልግሎት እንደሚሰጡ እና ለኢንቨስትመንት የሚመጣ ባለሀብት አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ አስፈላጊ ሂደቶችን አጠናቆ ወደ ስራ መግባት የሚችልበት እድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
ኢንቨስተሮች ከውጭ ለሚያመጧቸው ሰራተኞች የመኖሪያ ፈቃድ እንደሚሰጥም ነው የገለጹት፡፡ ሰራተኞችን በሚፈልጉበት ጊዜም በማህበራት አማካኝነት የሚፈልጉት የሰራተኛ አይነት እንደሚዘጋጅም ተናግረዋል፡፡ ለሰራተኞቻቸው ቤት መስራት ለሚፈልጉ ኢንቨስተሮች በጊቢው ዉስጥ ቦታ መዘጋጀቱንም አብራርተዋል፡፡
የመንግስት ትኩረት ግብርናውን በማዘመን የአርሶአደሩን ህይወት መቀየር እና ለወጣቶችም የስራ እድል መፍጠር በመሆኑ ኢንቨስተሮች ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጦ ኢንቨስትመንቱን ለማስፋፋት ለኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አቶ ብሩ በማብራሪያቸው አንስተዋል፡፡