ሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በፒተርስበርግ ተጠናቋል
አፍሪካ አዲስ የሀይል ማዕከል እየሆነች መምጣቷን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስታወቁ።
ላለፉት ሁለት ቀናት በፒተርስበርግ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ተጠናቋል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት በጉባኤው መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ሚና እያደገ መጥቷል ማለታቸውን አርቲ ዘግቧል።
"የምዕራባዊያን ሀገራት ተጽዕኖ በተቃራኒው እየቀነሰ መጥታል" ያሉት ፕሬዝዳንቱ "አፍሪካ አዲስ የሀይል ማዕከል እየሆነች ነው" ሲሉም አክለዋል።
ይሁንና በአፍሪካ አሁንም የቅኝ ግዛት አመለካከት አልተወገደም የሚሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን ይህ አመለካከት በቀድሞ ቅኝ ገዢ ሀገራት በግልጽ ይንጸባረቃልም ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር የበለጠ ተቀራርባ መስራት እንደምትፈልግ እና የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኑነቱ እያደገ እንደሚሄድም ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ ግንኙነቱ የጋራ ጥቅምን መሰረት ባደረገ መንገድ እንዲመራ ሩሲያ እና አፍሪካ የየራሳቸውን ሀላፊነቱ መወጣት እንዳለባቸውም ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።
ሩሲያ ከኡፍሪካ ጋር በሚኖራት የንግድ ግንኙነት በዶላር መገበያየት እንደማትፈልግም ፕሬዝዳንት ፑቲን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ሀገራት በራሳቸው እና ያመኑበትን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የልማት ፖሊሲዎችን የመከተል ነጻነት መከበር አለበት ብለዋል።
የስርዓተ ጾታ፣ ዲሞክራሲ እና ሰው ልማት ስም በታዳጊ ሀገራት ላይ የሚደረጉ ጫናዎችን መታገል ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን በሀገራት ላይ የሚጣሉ የተናጠል ማዕቀቦችንም ተቃውመዋል።
የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ የ49 ሀገራት ተወካዮች የተሳተፉበት ሲሆን ከተሳታፊዎች መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ የ17 ሀገራት ጠቅላይ ሚንስትር እና ፕሬዝዳንቶች ተሳትፈዋል።