ሰሜን ኮሪያ በነገው እለት 70ኛ አመት የድል በዓሏ ታከብራለች
በሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉ የተመራ ልኡክ ሰሜን ኮሪያ ገብቷል።
የሰሜን ኮሪያው መከላከያ ሚኒስትር ካንግ ሱን ናም እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በፒዮንግያንግ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ለሾጉ እና ልኡካቸው ደማቅ አቀባበል ማድረጋቸው ተዘግቧል።
በኮሮና ምክንያት ድንበሯን ዘግታ የቆየችው ሰሜን ኮሪያ የቻይና ልኡክንም ለመቀበል ተዘጋጅታለች።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው ሀገሪቱ በነገው እለት የምታከብረውን 70ኛ አመት የድል በዓል ደማቅ ለማድረግ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች።
የደቡብ ኮሪያው የዜና ወኪል ዮናፕም በኪም ሱንግ አደባባይ ለሚደረገው ወታደራዊ ትርኢት ከቀናት በፊት ዝግጅት መጀመሩን በሳተላይት ምስሎች መረጋገጡን ዘግቧል።
የሩሲያ እና ቻይና ከፍተኛ ባለስልጣናት በበዓሉ ላይ መታደም ፒዮንግያንግ ከሀገራቱ ጋር ስለመሰረተችው ጠንካራ ግንኙነት ማሳያ ተደርጎ እየተነሳ ነው።
ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን ጨምሮ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎቿን ታሳይበታለች ተብሎ የሚጠበቀው በዓል ለአሜሪካም ግልጽ መልዕክት መስደጃ ይሆናል ተብሏል።
ከ1950ው የኮሪያ ጦርነት ጀምሮ የሰሜን ኮሪያ አጋር የሆነችው ሞስኮ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ላይ ባለችበት ወቅት የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒዮንግያንግ ተገኝተዋል።
በኮሪያ ጦርነት ከደቡብ ኮሪያ ጎን የተሰለፈችው አሜሪካ ደግሞ ወደ ሴኡል በኒዩክሌር ሃይል የምትሰራ ግዙፍ መርከቧን ልካለች።
አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር ለምታደርገው ወታደራዊ ልምምድ ተደጋጋሚ የሚሳኤል ማስወንጨፍ አጻፋዊ እርምጃ የወሰደችው ሰሜን ኮሪያ ከዋሽንግተን ጋር ይበልጥ እየተራራቀች ነው።
የሩሲያ፣ ቻይና እና ሰሜን ኮሪያ ትብብርም የኮሪያ ልሳነ ምድርን ውጥረት ይበልጥ እንዳያንረው ስጋታቸውን የሚገልጹ ተንታኞች አሉ።
ሰሜን ኮሪያን ከየትኛውም ጥቃት ለመመከት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ሲገቡ የተደመጡት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በምዕራባውያን ለተገለለችው ሀገር አለሁ ካሉ ጥቂት ሀገራት መሪዎች አንዱ ናቸው።
ቻይናም ምንም እንኳን በዋሽንግተን እና ፒዮንግያንግ ፍጥጫ ዙሪያ እምብዛም አስተያየት መስጠት ባትወድም ለኪም ጆንግ ኡን ሀገር ድጋፍ ስታደርግ ይስተዋላል ይላል ፍራንሥ4 በዘገባው።
በተለይ የጸጥታው ምክርቤት በፒዮንግያንግ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ለመጣል የውሳኔ ሃሳብ ሲያቀርብ መቃወሟን በማውሳት።
ሰሜን ኮሪያ ከሶስት አመት የኮሮና እንቅስቃሴ ክልከላ በኋላ ለ70ኛ አመት የድል በዓሏ ድንበሯን ስትከፍትም ለወዳጆቿ ቤጂንግ እና ሞስኮ ቅድሚያ መስጠቷን ያብራራል።