ፕሬዝዳንት ፑቲን ሩሲያ በቅርቡ በጠቀለለቻቸው ግዛቶች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣሉን አስታወቁ
ሩሲያ አራት የዩክሬን ክልሎችን በህዝበ ውሳኔ ወደ ግዛቷ በይፋ እንደጠቀለለች በቅርቡ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል
ፑቲን፤ በአዋጁ መሰረት የኬርሰን፣ ዛፖሪዝያ፣ ዶኔትስክ እና ሉሃንስክ ገዥዎች ተጨማሪ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል ብለዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት በቅርቡ በጠቀለሏቸው ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣ’ሉ አስታወቁ፡፡
ፑቲን ውሳኔውን ያስወቁት በዛሬው እለት በሩሲያ ብሄራዊ ደህንነት ላይ የሚደርሱ ስጋቶችን ለመቅረፍ በሚል በተዘጋጀ የሩስያ የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
በአዋጁ መሰረት የኬርሰን፣ ዛፖሪዝያ፣ ዶኔትስክ እና ሉሃንስክ ገዥዎች ደህንነትን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ "አሁን ይህን አገዛዝ በሩሲያ ህግ ማዕቀፍ ውስጥ መደበኛ ማድረግ አለብን፤ ስለዚህ በእነዚህ አራት የሩሲያ ፌዴሬሽን ግዛቶች ላይ ወታደራዊ ሕግ መታወጁን ፊርሜያለሁ”ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
እንደ ኤኤፍፒ ዘገባ "የኪቭ መንግስት አካል ለመደራደር ፈቃደኛ ባለመሆኑ የሽብር ዘዴዎችን በመጠቀም ግዛታችንን እየደበደበ ነው"ም ብለዋል ፑቲን በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ባደረጉት ንግግር።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ ተለዋዋጭ እንደመሆኑ ለሁሉም ለውጦች ፈጣን ምላሽ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ፑቲን ሩሲያ አራት የዩክሬን ክልሎችን በህዝበ ውሳኔ ወደ ግዛቷ በይፋ እንደጠቀለለች መስከረም 30 ቀን 2022 ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡
ፕሬዝዳንቱ አራቱን ግዛቶች የሩሲያ አካል መሆናቸውን የሚያረጋግጠውን ፊርማቸውንም አኑሯል በወቅቱ፡፡
ከአሁን በኋላ እነዚህን ግዛቶች መንካት ማለት ሩሲያን መንካት ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር፡፡
ሩሲያ አራቱም ክልሎች መጠቅለሏ ይፋ ብታደረግም፤ የሞስኮ ድርጊት በአሜሪካም ሆነ በምዕራባውያን ተቀባይነት አላገኘም፡፡
የተባበሩት መንግስታት የዩክሬን ግዛቶችን “በኃይል ጠቅልላለች” ያላትን ሩሲያ ከቀናት በፊት ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤው ማውገዙ የሚታወስ ነው፡፡
ጉባዔው ሩሲያ አራት የዩክሬን ክልሎችን መጠቅለሏን ተከትሎ የጸጥታው ም/ቤት "ህገ-ወጥ" ነው ለተባለው ህዝበ ውሳኔ እውቅና እንዳይሰጥና ሩሲያ ጦሯን ከዩክሬን ምድር እንድታስወጣ የሚያስገድድ የውሳኔ ሃሳብ በከፍተኛ ድምጽ አጽድቋል፡፡
በዚህም መሰረት ከ193 አባላት ጠቅላላ ጉባኤ ውስጥ ሶስት አራተኛው ወይም 143 ሀገራት የዩክሬንን ሉዓላዊነት ፣ ነጻነት ፣ አንድነት እና የግዛት አንድነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁ ድንበሮች ውስጥ ያጸደቀውን ውሳኔ ደግፏል።
የጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ የሩስያ ወታደሮች እንደፈረንጆቹ የካቲት 24 በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመሩ በኋላ ካጸደቃቸው አራት የውሳኔ ሃሳቦች አንጻር ሲታይ ለሩሲያ “ ከፍተኛው ተግሳጽ” ነው ተብሏል፡፡