አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሀገራት፣ ፑቲን ሩሲያ በዩክሬን ለምታካሂደው ዘመቻ ሙሉ ድጋፍ ወደ ሰጧት ሰሜን ኮሪያ የሚያደርጉትን ጉብኝት በአንክሮ እየተከታተሉት ነው
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሰሜን ኮሪያ ገብተዋል።
ፕሬዝደንት ፑቲን በዛሬው እለት ፒዮንግያንግ ሲገቡ ደማቅ የተባለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሀገራት፣ ፑቲን ሩሲያ በዩክሬን ለምታካሂደው ዘመቻ ሙሉ ድጋፍ ወደሰጠችው ሰሜን ኮሪያ የሚያደርጉትን ጉብኝት በአንክሮ እየተከታተሉት ነው።
ከ24 አመት በኋላ ወደ ፒዮንግያንግ ያቀኑትን ፕሬዝደንት ለመበቀበል በኪም ሁለተኛ አደባባይ በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ ወጥቶ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህን ተከትሎ ፑቲን እና ኪም ንግግር ለማድረግ ወደ ኩምሱሳን ቤተመንግሥት አቅንተዋል።
"ሩሲያ በዩክሬን የምታካሄደውን ዘመቻ ጨምሮ ለሩሲያ ፓሊሲ ያለውን ወጥ ድጋፍ በእጅጉ እናደንቃለን" ሲሉ ፑቲን በውይይቱ መጀመሪያ ላይ መናገራቸውን ሮይተርስ የየሩሲያውን ሪያ ዜና አገልግሎት ጠቅሶ ዘግቧል።
ፑቲን ሩሲያ የኢምፔሪያሊስቷ አሜሪካ እና አጋሮቿን የበላይነት እየተዋጋች ነው ብለዋል።
ኪም በበኩላቸው የሰሜን ኮሪያ-ሩሲያ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን ገልጸዋል።
"አሁን ላይ የአለም ሁኔታ የበለጠ እየተወሳሰበ እና በፍጥነት እየተቀየረ ነው። በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ከሩሲያ ጋር ያለንን ግንኙን የበለጠ እናጠናከራለን" ብለዋል።
ኪም አክለውም ሰሜን ኮሪያ "ሩሲያ ሉአላዊነቷን እና ደህንነቷን ለመጠበቅ በዩክሬን የምታደርገውን ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ሙሉ ሙሉ እንደግፋለን" ሲሉም ተናግረዋል።
ምዕራባውያን ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ በዩክሬን ለምታደርጠው ጦርነት ጥቅም ላይ የሚውል የጦር መሳሪያ ታቀርባለች ሲሉ ይከሷታል። ሰሜን ኮሪያ ግን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ነው በማለት በተደጋጋሚ አጣጥላዋለች።