ፑቲን ከ24 አመት በኋላ ዛሬ በሰሜን ኮሪያ ጉብኝት ያደርጋሉ
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ከፒዮንግያንግ ጋር “ከምዕራባውያን ቁጥጥር ውጭ የሆነ” የንግድ እና ደህንነት ስርአት እንገነባለን ብለዋል
አሜሪካ የሁለቱ ሀገራት ትብብር እያደገ መሄድ አሳሳቢ መሆኑን አስታውቃለች
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከ24 አመት በኋላ ዛሬ በሰሜን ኮሪያ ጉብኝት ያደርጋሉ።
ፕሬዝዳንቱ ከጉብኝታቸው አስቀድሞ በላኩት ደብዳቤ ሰሜን ኮሪያ ሞስኮ በዩክሬን የምታካሂደውን ጦርነት “በጽኑ መደገፏን” ማድነቃቸውን የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
ሀገራቸው ከፒዮንግያንግ ጋር “ከምዕራባውያን ቁጥጥር ውጭ የሆነ” የንግድ እና ደህንነት ስርአት እንደምትገነባ መናገራቸውንም ነው ዘገባው የጠቆመው።
ዛሬ በፒዮንግያንግ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር የሚገናኙት ፑቲን፥ ሰሜን ኮሪያ “የአሜሪካን ጫና፣ ማጭበርበርና ወታደራዊ ስጋት” ለመመከት የምታደርገውን ጥረት ሞስኮ እንደምትደግፍ መናገራቸውንም የሰሜን ኮሪያው ገዥ ፓርቲ ልሳን የሆነው ሮዶንግ ሲንሙን አስነብቧል።
ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ በመከባበር ላይ የተመሰረተ ባለብዙ ወገን አለም እንዳይፈጠር መሰናክል እየፈጠሩ ናቸው ያሏቸውን ምዕራባውያን አጥብቀው መቃወማቸውን ይቀጥላሉም ነው ያሉት።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ባለፈው መስከረም ወር በሩሲያዋ ቮስቶችኒ ኮስሞድሮም ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።
ፑቲን ግን በሰሜን ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ጉብኝት ያደረጉት በፈረንጆቹ በ2000 እንደነበር ሬውተርስ አስታውሷል።
በዚህ “የወዳጅ” ጉብኝታቸውም ከኪም ጋር በደህንነት እና ሌሎች ጉዳዮች የትብብር ስምምነት እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል ብሏል ክሬምሊን።
ፒዮንግያንግ በኪም ኢል ሱንግ አደባባይ ለፑቲን ደማቅ አቀባበል ለማድረግና ወታደራዊ ትርኢት ለማቅረብ መዘጋጀቷ ተሰምቷል።
ኪም ባለፈው ሳምንት የሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ግንኙነት “ማንም የማይበጥሰው” ደረጃ መድረሱን መናገራቸው አይዘነጋም።
አሜሪካ በበኩሏ የሀገራቱ ትብብር እያደገ መሄድ እንደሚያሳስባት ገልጻለች።
የሀገሪቱ ብሄራዊ የደህንነት ምክርቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ፥ “የሚያሳስበን የፑቲን ጉብኝት ሳይሆን የሀገራቱ ግንኙነት በየጊዜው እያደገ መሄዱ ነው” ብለዋል።
ዋይትሃውስ ሩሲያ በዩክሬን በምታካሂደው ጦርነት የፒዮንግያንግ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፤ ሞስኮም ለሰሜን ኮሪያ የስፔስ ቴክኖሎጂ ድጋፍ እያደረገች ነው የሚሉ ክሶችን ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወቃል።
ፑቲንም ሆነ ኪም የዋሽንግተንን ክስ ባይቀበሉትም ሁለቱ ሀገራት የምዕራባውያኑን ማዕቀብ እና ጫና በትብብር ለመፍታት የሚያስችል ግንኙነት በመመስረት ላይ ናቸው።