ደቡብ ኮሪያ ወደ ሰሜን ኮሪያ የማስጠንቀቂያ ተኩስ ተኮሰች
ይህ ክስተት የተፈጠረው ፒዮንግያንግ ለከዳተኞች "ስጦታ" ይሆናል ያለችውን ቆሻሻ የያዙ 600 ፊኛዎችን ወደ ደቡብ ኮሪያ ከላከች በኋላ ነው
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በግልጽ ድንበር ከጣሱ በኋላ የደቡብ ኮሪያ ጦር የማስጠንቀቂያ ተኩስ ማሰማቱን የሴኡል ባለስልጣናት ተናግረዋል
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በግልጽ ድንበር ከጣሱ በኋላ የደቡብ ኮሪያ ጦር የማስጠንቀቂያ ተኩስ ማሰማቱን የሴኡል ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የደቡብ ኮሪያ ጆይንት ቺፍ ኦፍ ስታፍ(ጄሲኤስ)ባለፈው እሁድ እለት ከጦር ነጻ በሆነው ቀጣና(ዲኤምዜድ) ውስጥ የነበሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወታደሮች ድንበር ማለፋቸውን በዛሬው እለት ተናግሯል።
የጄሲኤስ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ሊ ሰንግ ጁን ቦታው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ በመሆኑ እና የድንበር ምልክቶችን ስለሚሸፍን ጥሰቱ ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ነው ብሎ ጦሩ እንደማያስብ ገልጸዋል።
"የእኛ ጦር ማስጠንቀቂያ ካሰሟ እና የማስጠንቀቂያ ተኩስ ከከፈተ በኋላ ወታደሮቹ ወዲያውኑ ተመልሰዋል" ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ድንበር አቋርጠዋል የተባሉት ወታደሮች ቁጥራቸው ከ20-30 ሊሆን እንደሚችል ሮይተርስ ዮንሀፕ የተባለውን ዜና አገልግሎትን ጠቅሶ ዘግቧል።
ይህ ክስተት የተፈጠረው ፒዮንግያንግ ለከዳተኞች "ስጦታ" ይሆናል ያለችውን ቆሻሻ የያዙ 600 ፊኛዎችን ወደ ደቡብ ኮሪያ ከላከች በኋላ ነው።
ይህን ተከትሎም ሴኡል በፈረንጆቹ 2018 በተካሄደው ታሪካዊ በተባለው የኢንተር ኮሪያ ጉባኤ ላይ የተደረሰውን ስምምነት በማቋረጥ ድንበር አካባቢ ወታራዊ እንቅስቃሴዎችን እያካሄደች ትገኛለች።
ሴኡል የፒዮግያንግን ድርጊት "የማይረባ እና አደገኛ" ስትል ነበር የገለጸችው።
የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች ከዚህ በፊት ድንበር በሚያቋርጡ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ላይ የማስጠንቀቂያ ተኩስ ሲያሰሙ የመጀመሪያቸው አይደለም። ነገርግን ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ተግባር የሚያጋጥመው ፒዮንግያንግ የይገባኛል ጥያቄ በምታነሳበት የማሪታይም ድንበር ነው።