ፑቲን እና ፕሪጎዥን ከአመጹ በኋላ በክሬምሊን መምከራቸው ተነገረ
ውይይቱ የተካሄደው ዋግነር ከተማ ተቆጣጥሮ አመጽ ካወጀ ከአምስት ቀናት በኋላ ነው ብለዋል የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ
ሶስት ስአት በወሰደው ምክክር 35 የዋግነር ከፍተኛ አዛዦችም ተሳትፈው እንደነበር ተገልጿል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዋግነር ቡድን መሪው ይቪግኒ ፕሪጎዥን ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተነገረ።
ፑቲን ከፕሪጎዥን ጋር በክሬምሊን የመከሩት ከዋግነር አመጽ አምስት ቀናት በኋላ እንደነበር የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በዛሬው እለት አስታውቀዋል።
በውይይቱ ከፕሪጎዥን ባሻገር 35 የቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድኑ ከፍተኛ አዛዦችም መሳተፋቸውን ነው ፔስኮቭ ያረጋገጡት።
ሶስት ስአት ወስዷል በተባለው ምክክርም ፑቲን በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ዙሪያ ማብራሪያ መስጠታቸውን ቃልአቀባዩን ጠቅሶ አርቲ አስነብቧል።
ፕሬዝዳንቱ ሰኔ 24 በተፈጸመው የዋግነር ድርጊት ዙሪያም ከቡድኑ አዛዦች ገለጻ እንደተደረገላቸውና ምክክር እንደተደረገበት ተገልጿል።
የዋግነር መሪው ፕሪጎዥን በዚሁ ወቅትም ለፑቲን ያልተገደበ ድጋፍ እንደሚሰጥ መግለጹን ነው ዲሚትሪ ፔስኮቭ የተናገሩት።
የዋግነር አመጽ በ24 ስአት ውስጥ መቋጫ አግኝቶ ፕሪጎዥንም በቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አደራዳሪነት ወደ ቤላሩስ እንዲያመሩ ከተደረገ ከአምስት ቀናት በኋላ ነው ፑቲን እና የዋግነር አዛዦች በክሬምሊን የተገናኙት።
ፕሪጎዥን በአሁኑ ወቅት የት እንደሚገኝ በይፋ አልተገለጸም።
የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንድር ሉካሼንኮ ከሶስት ቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ግን ግለሰቡ በሩሲያ ውስጥ እንደሚገኝ መናገራቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የረጅም አመት ትውውቅ ያለው ፕሪጎዥን የፑቲን ምግብ አብሳይ ወይም ሼፍ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ዋግነር በዩክሬን ጦርነት በነበረው ተሳትፎ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉ እና ባልደረቦቻቸውን በተደጋጋሚ ሲወቅስና ሲዝትባቸውም ስለፑቲን አንድም ጊዜ መጥፎ ነገር ተናግሮ አያውቅም ተብሏል።
ከቤላሩስ ሸምጋይነት በኋላ የሽብር ክሱ የታጠፈለት ይቪግኒ ፕሪጎዥን ቅጥረኛ ወታደሮችን ዳግም መመልመል መጀመሩም ተዘግቧል።