የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ከሁለት ሳምንት በፊት በሩሲያ ጦር ላይ ማመጹን ተከትሎ የመፈንቅለ መንግሥት ክስ ቀርቦበት ነበር
የዋግነር አዛዥ የቨግኒ ፕሪጎዚን ከቤላሩስ ወደ ሩሲያ ተመለሱ።
ዋግነር የተሰኘው የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ከሁለት ሳምንት በፊት የሩሲያ ጦር ጥቃት አደረሰብኝ በሚል በሀገሪቱ ጦር ላይ ጥቃት ከፍቶ ነበር።
ይህን ተከትሎም ከሩሲያ ጦር ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና መንግስታቸው የመፈንቅለ መንግሥት ክስ ተመስርቶበት ነበር።
ፕሬዝዳንቱ ፑቲንም በዋግነር ወታደራዊ ቡድን አዛዥ በሆኑት የቨግኒ ፕሪጎዚን እና ወታደሮቻቸው ላይ ጥቃት እንዲከፈትባቸው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሌኮሼንኮ ባደረጉት ድርድር በፕሪጎዚን ላይ የተመሰረተው ክስ ውድቅ እንዲደረግ እና አዛዡም ወደ ቤላሩስ እንዲዛወሩ ከስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።
የዋግነር ቡድን አባላትም ከሩሲያ መከላከያ ጋር የስራ ውል እንዲፈራረሙ እና አዛዡ የነበሩት ፕሪጎዚን ወደ ሚንስክ እንዲጓዙ በተደረሰው ስምምነት መሰረት አዛዡ ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ እለት ወደ ቤላሩስ ገብተዋው ነበር።
ቢቢሲ በሰበር ዜናው እንደዘገበው ከሆነ ቤላሩስ የነበሩት የዋግነር አዛዥ ፕሪጎዚን ወደ ሩሲያ ተመልሰዋል።
የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሌኮሼንኮ እንዳሉት ከሆነ ወደ ሀገራቸው ገብተው የነበሩት ፕሪጎዚን እና ወታደሮቻቸው ወደ ሩሲያዋ ፒተርስበርግ ከተማ ተመልሰዋል ብለዋል።
ይሁንና የዋግነር አዛዡ ለምን እንደተመለሱ፣ ስለ ዋግነር ቀጣይነት እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዋግነር በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ አንድ ቢሊዮን ዶላር አንዱተሰጣቸው ገልጸው በሩሲያ ላይ ክህደት መፈጸሙን ገልጸዋል።
ዋግነር እንዲፈርስ ወስነናል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ወታደሮቹ ፈቃደኞች ከሆኑ ከሩሲያ ጦር ጋር የስራ ስምምነት እንደሚፈርሙ እና ከዚህ በፊት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ዋግነር ያደረጋቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶች እና ትብብሮች ይቀጥላሉም ብለዋል።