የሩሲያው ዋግነር ወታደራዊ ቡድን አሁንም ተዋጊዎችን እየመለመለ መሆኑ ተገለጸ
ፕሬዝዳንት ፑቲን ዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን እንዲፈርስ ወስነናል ማለታቸው ይታወሳል
ቤቨግኒ ፕሪጎዚን የሚመራው ዋግነር ከአንድ ሳምንት በፊት መፈንቅለ መንግስት በመፈጸም ወንጀል መከሰሱ ይታወሳል
የሩሲያው ዋግነር ወታደራዊ ቡድን አሁንም ተዋጊዎችን እየመለመለ መሆኑ ተገለጸ።
ዋግነር የተሰኘው የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ከአንድ ሳምንት በፊት የሩሲያ ጦር ጥቃት ከፈተብኝ በሚል መፈንቅለ መንግስት መሞከሩ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዋግነር እንዲፈርስ መወሰናቸውን እና የጦር አባላቱም ከሩሲያ መከላከያ ጋር የስራ ስምምነት እንዲፈጽም አድርገናል ብለውም ነበር።
ይሁንና እንዲፈርስ የተወሰነበት ዋግነር አሁንም አዳዲስ ተዋጊዎችን እየመለመለ እና ስምምነቶችን ከፈቃደኞች ጋር እየተፈራረመ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን አክለውም ከዚህ በፊት ከዋግነር ወታደራዊ ቅጥረኛ ቡድን ጋር የተደረጉ ስምምነቶች ይቀጥላሉ ማለታውቸም አይዘነጋም።
በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የተከሰሱት የዋግነሩ አዛዥ ከሩሲያ ጦር ጋር የጀመሩትን ውጊያ እንዲያቆሙ፣ የተመሰረተባቸው ክስ ውዲቅ እንዲደረግ እና ወደ ቤላሩስ እንዲያመሩ መስማማታቸው ተገልጿል።
በዚህ ስምምነት መሰረትም የፕሪጎዚን የግል ጄት ባሳለፍነው ማክሰኞ ቤላሩስ አርፋለች የተባለ ሲሆን በዚያው ቀን ምሽት ደግሞ ይህች ጀት ወደ ሞስኮ መብረሯ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ዋግነር ለአንድ ተዋጊው በወር 2 ሺህ ዶላር ይከፍላል የተባለ ሲሆን ከሩሲያ ጦር ጋር የገባበት ግጭት እውነት ላይሆን ይችላል እየተባለም ይገኛል።
በርካቶች ለዚህ መደምደሚያ የበቁት ዋግነር አሁንም ምልመላውን መቀጠሉ፣ አይደለም መፈንቅለ መንግስት ቀላል ትችቶችን በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ የሰነዘሩ ለዓመታት ወደ እስር ቤት እየተጣሉ እንዴት ፕሪጎዚን ይቅር ተባሉ ሲሉ በማስረጃነት እያነሱ ነው ተብሏል።