ፕሬዝዳንት ፑቲን ዩክሬናውያን ህጻናትን ወደ ሩሲያ አስገድዶ በመውሰድ በአይሲሲ የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን በከፈቱት ጦርነት ለፍትህ መቅረብ እንዳለባቸው የዩክሬን አቻቸው ቮልድሚር ዜለንስኪ ተነገሩ።
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ በኔዘርላንድስ ዘ ሄግ የሚገኘውን የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትን ዛሬ ጎብኝተዋል።
ከጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ፥ “እነዚህ ሰዎች(ፑቲን) የማይነኩ አካላት አለመሆናቸውን ማሳየት አለብን፤ ፍትህ እንሻለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
“የሩሲያን ወረራ የሚመለከት ልዩ ችሎት ሊቋቋም ይገባል”ም ነው ያሉት።
ይሁን እንጂ የሀገራት ወረራን የተመለከቱ ጉዳዮችን በሄግ የሚገኘው ፍርድ ቤት የመዳኘት ስልጣን የለውም ተብሏል።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በበኩሉ የዩክሬን ወረራ እና ተያያዥ የወንጀል ድርጊቶችን የሚመለከት ራሱን የቻለ አለምአቀፍ የዳኞች ቡድን በአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ስር እንዲቋቋም ጠይቋል።
ይቋቋም የተባለው ችሎት የሚያሳልፈው ውሳኔስ በሀገራት ድጋፍ ወይስ በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ተፈጻሚ ይሆናል የሚለው ግን አከራካሪ ጉዳይ ሆኗል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ግን “በርግጠኝነት ስለምናሸንፍ የሚፈጠረውን እናያለን” ሲሉ ፑቲን ለፍትህ መቅረባቸው እንደማይቀር ተስፋቸውን ገልጸዋል።
አይሲሲ ባለፈው መጋቢት ወር ፑቲን በዩክሬን ህጻናትን አገድደው ወደ ሩሲያ እንዲገቡ አድርገዋል በሚል የእስር ማዘዣ እንዳወጣባቸው የሚታወስ ነው።
የፍርድ ቤቱ አባል ያልሆነችው ሞስኮ፥ የወንጀለኞች ፍርድ ቤቱ ምዕራባውያን ያልፈለጉትን አካል የሚያሳድዱበት እንጂ የእውነት ፍትህን የሚያሰፍን እንዳልሆነ ትገልጻለች።
በዩክሬን ፈጽማዋለች ተብላ የሚቀርብባትን የአለማቀፍ ወንጀል ድርጊቶችም አትቀበላቸውም።