ሩሲያ፤ አሜሪካና ዩክሬን በክሬምሊን ላይ የተፈጸመውን የድሮን ጥቃት ውድቅ ማድረጋቸው "አስቂኝ ነው" አለች
ሩሲያ በክሬምሊን ላይ ከደረሰው ጥቃት ጀርባ የአሜሪካ እጅ እንዳለ በሚገባ እናውቃለን ብላለች
“በክሬምሊን ቤተ መንግስት ጥቃት ላይ የተሳተፉ ሁሉ ከባድ ቅጣት ይጠብቃቸዋል” ስትል ሩሲያ ዝታለች
በትናንትናው እለት በሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መኖሪያ በሆነው የክሬምሊን ቤተ መንግስት ላይ የድሮን ጥቃት ለመፈጸም ሙከራ መደረጉ ተገልጿል።
ሩሲያ፥ ዩክሬን ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲንን ለመግደል በክሬምሊን ቤተ መንግስት ላይ የድሮን ጥቃቶችን ለመፈጸም ሙከራ አድርጋለች በሚል ከሳለች።
በተጨማሪም አሜሪካ ከጥቃቱ ጀርባ አለች ሲል የሩሲያው ክሬምሊን ቤት መንግስት ከሷል።
ዩክሬንም ይሁን አሜሪካ በክሬምሊን ቤተ መንግስት ጥቃት ላይ እጃቸው አለበት መባሉን ባወጡት ግለጫ ውድቅ አድርገዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ሀገራቸው በሞስኮ እና በፕሬዚዳንቷ ላይ ጥቃት አላደረሰችም ሲሉ የቀረበባቸውን አስተባብለዋል።
አሜሪካ በበኩሏ የክሬምሊኑን ጥቃት በተመለከተ መረጃው ደርሶኛል፤ ትክክለኛውን ጥቃት አድራሽ እና አላማውን ግን ማረጋገጥ አልቻልኩም ብላለች።
ይህንን ተከትሎ ክሬምሊን ቤት መንግስት ባወጣው መግለጫ፤ አሜሪካና ዩክሬን በክሬምሊን ላይ የተፈጸመውን የድሮን ጥቃት ውድቅ ማድረጋቸው "አስቂኝ ነው" ብሏል።
አሜሪካ ከዚህ ጥቃት ጀርባ እንዳለችም ጠንቅቀን እናውቃለን ነው ክሬምሊን በመግለጫው።
የቤተ መንግስቱ ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ በሰጡት መግለጫ፥ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሁን ላይ ስራቸውን ከክሬምሊን ቤተ መንግስት ሆነው እየሰሩ መሆኑን አስታውቋል።
ሞስኮ በአጸፋ ለምትወስደው እርምጃ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ዋነኛ ኢላማ ስለመሆናቸው ግን ከማሳወቅ ተቆጥቧል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ፤ በክሬምሊን ቤተ መንግስት ጥቃት ላይ የተሳተፉ በሙሉ እንደሚለቀሙ እና ከባድ የቅጣት እንደሚቀበሉ እርግጠኛ ነኝ ሲል ዝቷል።
በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መኖሪያ ክሬምሊን ቤተመንግስት የተቃጣው የድሮን ጥቃት ሞስኮን ክፉኛ አስቆጥቷል።
የሀገሪቱ የደህንነት ምክርቤት ምክትል ሊቀመንሩ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ትናንት በሰጡት አስተያየት፥ ጥቃቱ ሩሲያ ቮልድሚር ዜለንስኪ እና ግብረአበሮቹን ከማስወገድ ውጭ ሌላ አማራጭ አሳጥቷታል ነው ያሉት።
የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት በኬቭ ላይ ሊወሰድ የሚችለው የአጻፋ እርምጃ የበረታ እንደሚሆን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ይህንን ተከትሎም በዛሬው እለት በዩክሬን ዋና ከተማዋ ኪቭን ጨምሮ በዜፖሬዢያ እና በኦዴሳ ከተሞች ከፍተኛ ፍንዳታዎች መሰማታቸው ተነግሯል።