በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የግድያ ሙከራ ተፈጸመ
ሩሲያ፥ ዩክሬን ፑቲንን ለመግደል ክሬምሊን ላይ የድሮን ጥቃቶችን ለመፈጸም ሙከራ አድርጋለች በሚል ከሳለች
ዩክሬን በበኩሏ የድሮን ጥቃት ክሱን "ድራማዊ ውንጀላ" ነው ብላዋለች
በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የግድያ ሙከራ ተፈጸመ፡፡
ከተጀመረ 15 ወራት የሞላው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን ማስተናገዱን ቀጥሏል፡፡
በሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መኖሪያ በሆነው የክሬምሊን ቤተ መንግስት ላይ የድሮን ጥቃት ለመፈጸም ሙከራ መደረጉ ተገልጿል፡፡
እንደ ራሺያ ቱዴይ ዘገባ ከሆነ የድሮን ጥቃቱ ያነጣጠረው በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ በስፍራው እንዳልነበሩ ተጠቅሷል፡፡
የቤተ መንግስቱ ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ፥ ጥቃቱን በሁለት ድሮኖች ለመፈጸም ጥረት ቢደረግም የሩሲያ ጦር በወሰደው እርምጃ ድሮኖቹ መመታታቸውን ተናግረዋል።
በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ድሮኖቹ በክሬምሊን ዙሪያ ተመተው ሲወድቁ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ተለቀዋል።
ድሮኖቹ የየት ሀገር ስሪት እንደሆነ እስካሁን ባይታወቅም ሞስኮ ከሽፏል ለተባለው ሙከራ ኬቭን ተጠያቂ አድርጋለች።
በድሮኖቹ ጥቃት የተጎዳ ሰው አለመኖሩን የተናገሩት ቃል አቀባዩ ሞስኮ ለኬቭ የግድያ ሙከራ አጻፋውን እንደምትመልስ ዝተዋል።
የሞስኮ ከተማ ከንቲባ በበኩላቸው በከተማዋ ከተፈቀደላቸው የደህንነት ተቋማት ውጪ የድሮን እንቅስቃሴ መታገዱን ገልጸዋል፡፡
ፊንላድን እየጎበኙ ያሉት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ከሄልስንኪ በክሪምሊን ቤተ መንግስት ላይ ተፈጸመ ስለተባለው የድሮን ጥቃት መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ አክለውም ዩክሬን በሩሲያ የተወሰደባትን ሁሉንም ግዛቶች ለማስመለስ ያላትን ሀይል ሁሉ ማሰማራቷን ተናግረዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንታዊ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫም፥ ዩኪረን ክሬምሊን ላይ ተቃጣ ከተባለው የድሮን ጥቃት ጋር ምንም ግንኙነት የላትም፤ ድራማዊ ውንጀላ ነው በሚል ክሱን አስተባብሏል።