ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ “ዩክሬን በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ የግድያ ሙከራ አላደረገችም” አሉ
ሩሲያ፥ ዩክሬን ፑቲንን ለመግደል ክሬምሊን ላይ የድሮን ጥቃቶችን ለመፈጸም ሙከራ አድርጋለች በሚል ከሳለች
የዩክሬኗ ዋና ከተማ ኪቭን ጨምሮ በርካ ተከሞች በፍንዳታ እየተናጡ ነው
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ሀገራቸው “በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ የግድያ ሙከራ አላደረገችም” አሉ።
በትናንትናው እለት በሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መኖሪያ በሆነው የክሬምሊን ቤተ መንግስት ላይ የድሮን ጥቃት ለመፈጸም ሙከራ መደረጉ ተገልጿል፡፡
ሩሲያ፥ ዩክሬን ፕሬዝዳት ቪላድሚር ፑቲንን ለመግደል በክሬምሊን ቤተ መንግስት ላይ የድሮን ጥቃቶችን ለመፈጸም ሙከራ አድርጋለች በሚል ከሳለች።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው ሀገራቸው በሞስኮ እና በፕሬዚዳንቷ ላይ ጥቃት አላደረሰችም ሲሉ የቀረበባቸውን አስተባብለዋል።
“ፕሬዝዳንት ፑቲንንም ይሁን ሞስኮን አላጠቃንም” ያሉት ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ “እየተዋጋን ያለነው በራሳችን ድንበር ላይ ነው፤ ከተሞቻችን እና መንደሮቻችንን ከወራሪዎች እንጠብቃለን ሲሉም ተናግረዋል።
የክሬምሊን ቤተ መንግስት ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ ትናንት በሰጡት መግለጫ፥ ሞስኮ ለኬቭ የግድያ ሙከራ አጻፋውን እንደምትመልስ መዛታቸው ይታወሳል።
በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መኖሪያ ክሬምሊን ቤተመንግስት የተቃጣው የድሮን ጥቃት ሞስኮን ክፉኛ አስቆጥቷል።
የሀገሪቱ የደህንነት ምክርቤት ምክትል ሊቀመንሩ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ትናንት በሰጡት አስተያየት፥ ጥቃቱ ሩሲያ ቮልድሚር ዜለንስኪ እና ግብረአበሮቹን ከማስወገድ ውጭ ሌላ አማራጭ አሳጥቷታል ነው ያሉት።
የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት በኬቭ ላይ ሊወሰድ የሚችለው የአጻፋ እርምጃ የበረታ እንደሚሆን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ይህንን ተከትሎም በዛሬው እለት በዩክሬን ዋና ከተማዋ ኪቭን ጨምሮ በዜፖሬዢያ እና በኦዴሳ ከተሞች ከፍተኛ ፍንዳታዎች መሰማታቸው ተነግሯል።
ሩሲያ ዩክሬንን ተጠያቂ ያደረገችበትና ፕሬዝዳንት ፑቲንን ለመግደል ያለመ ነው ያለችውን የድሮን ጥቃት ማክሸፏን መግለጿ ይታወሳል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ግን ኬቭ ከጥቃቱ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላት ተናግረዋል።
አሜሪካ በበኩሏ የክሬምሊኑን ጥቃት በተመለከተ መረጃው ደርሶኛል፤ ትክክለኛውን ጥቃት አድራሽ እና አላማውን ግን ማረጋገጥ አልቻልኩም ብላለች።