ፑቲን ሩሲያ በወታደሮች ብዛት ከአሜሪካ እና ህንድ እንድትበልጥ አዘዙ
ፕሬዝዳንቱ 180 ሺህ ምልምሎች የሩሲያን ጦር እንዲቀላቀሉ ማዘዛቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ ወታደሮች ቁጥር 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ይደርሳል
ፑቲን በዩክሬን ጦርነት ከጀመሩ ወዲህ የሀገሪቱን ወታደሮች ቁጥር ሶስት ጊዜ አሳድገዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሀገራቸው መደበኛ ጦር ቁጥር በ180 ሺህ እንዲያድግ ትዕዛዝ ሰጡ።
በክሬምሊን ድረገጽ ላይ የወጣው መመሪያ ፑቲን አጠቃላይ የሩሲያ ጦር ሃይል ወደ 2 ነጥብ 38 ሚሊየን እንዲያድግ ማሳሰባቸውንና ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 5 ሚሊየኑ ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ወታደሮች እንደሚሆኑ ያመላክታል።
ፕሬዝዳንቱ ያሳለፉት መመሪያ ሩሲያን ከቻይና በመቀጠል በአለማችን በርካታ ወታደሮች ያሏት ሀገር ያደርጋታል።
ቤጂንግ 2 ሚሊየን መደበኛ ወታደሮች እንዳሏት የአለማቀፉ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ጥናት ተቋም (አይአይኤስኤስ) መረጃ ያመለክታል።
የሩሲያ ጦር ተጨማሪ 180 ሺህ ወታደሮችን ሲያካትት በወታደሮች ብዛት አሜሪካ እና ህንድን እንደሚቀድምም ነው የተገለጸው።
ፑቲን በዩክሬን ጦርነት ካወጁበት የካቲት 2022 ወዲህ የሀገራቸው ወታደሮች ብዛት እንዲጨምር ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
ውሳኔው ሩሲያ ምንም እንኳን ከዩክሬን በሶስት እጥፍ የሚበልጥ ህዝብ እና በርካታ ወታደሮች ቢኖራትም ሶስተኛ አመቱን ከወራት በኋላ የሚይዘው ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰባት አመላካች ነው ተብሏል።
የሩሲያ የታችኛው ምክርቤት የመከላከያ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አንድሬ ካርታፖሎቭ ግን የወታደሮች ቁጥር እንዲጨምር የተወሰነው ወቅታዊውን አለማቀፋዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ነው ብለዋል።
ከሩሲያ ጋር የምትዋሰነው ፊንላንድ የኔቶ አባል መሆኗን በመጥቀስም በሰሜን ምዕራብ ሩሲያ ተጨማሪ ሃይል ማሰማራት ማስፈለጉን አብራርተዋል።
ሩሲያ ከዩክሬኑ ጦርነት መጀመር በኋላ በተከታታይ 137 ሺህ እና 170 ሺህ ወታደሮች ጦሩን እንዲቀላቀሉ አድርጋለች።
በ2022 በመስከረም እና ጥቅምት ወር ተጨማሪ 300 ሺህ ወታደሮችን ለመመልመል ጥሪ ማቅረቧን ተከትሎም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ሀገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ክሬምሊን በአሁኑ ወቅት አስገዳጅ ብሄራዊ ውትድርና የለም ያለ ሲሆን፥ በዩክሬን ለመዋጋት ፍላጎት ያላቸው ሩሲያውያን ጦሩን ይቀላቀላሉ ብሏል።
የወታደሮቹ ቁጥር መጨመር ሩሲያ በምስራቃዊ ዩክሬን ለምታደርገው ግስጋሴ እና በኩርስክ ክልል የገቡ የዩክሬን ወታደሮችን ለማስወጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኖበታል።