የዩክሬን ጦር በሚከዱ ወታደሮች ቁጥር መጨመር ችግር ላይ እንደሚገኝ ተነገረ
በ2024 የመጀመርያ ወራት ብቻ ከውግያ ቦታዎች የጠፉ 19 ሺ ወታደሮች በሀገር ክህደት ክስ ተከፍቶባቸዋል
ወታደሮች ሁለት አመት ተኩል በቆየው ጦርነት በመሰላቸታቸው የውግያ ተነሳሽነታቸው ቀንሷል ተብሏል
ዩክሬን ከጦር ግንባሮች በሚከዱ ወታደሮች ቁጥር መጨመር ችግር ውስጥ እንደምትገኝ ተነገረ፡፡
ከጦር መሳርያ እና ከተዋጊዎች እጥረት ባለፈ በከዳተኛ ወታደሮች ጦሩ እየተፈተነ እንደሚገኝ ሲኤንኤን ያናገራቸው የጦር መሪዎች ተናግረዋል፡፡
ሲኤንኤን ያነጋገራቸው በምስራቅ ዩክሬን እና በፖክሮቭስክ የውግያ ቀጠናዎች እያዋጉ የሚገኙ 6 የጦር መሪዎች በርካታ ወታደሮቻቸው ከግንባር ላይ እንደሚከዱ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በጦሩ መካከል የበላይ አለቆችን ትዕዛዝ አለማክበር እና አለመታዘዝ እየተስፋፋ ይገኛል ነው የተባለው፡፡
ሁለት አመት ተኩል የቆየው ጦርነት የወታደሮች የመወጋት ሞራል እንዲቀንስ እንዲሁም እንዲሰላቹ አድርጓል ያሉት አዛዦቹ ከዚህ ባለፈ አዲስ ተመልምለው የሚመጡ ወታደሮች ደግሞ የጦርነቱን ጫና መቋቋም ባለመቻላቸው ከውግያ ስፍራዎች በመክዳት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በጦርነቱ ጅማሮ በፈቃደኝነት ጦሩን የተቀላለቀሉት የተሻለ የውግያ ተነሳሽነት ሲኖራቸው ሀገሪቷ ባወጣችው የብሔራዊ አገልግሎት ተመልምለው የመጡት አዲስ ወታደሮች ግን በጦርነቱ የመሳተፍ ፍላጎት ስለሌላቸው በውግያ ላይ ያላቸው አፈጻጸምም ዝቅተኛ ነው ተብሏል፡፡
በዚህ የነተሳም የተለያዩ ሻለቃዎች እና ብርጌዶች በተበታተነ ሁኔታ ውግያው ውስጥ እንዲገቡ በርካታ ጉዳትም እንዲደርስ ምክንያት መሆኑ ነው የተነገረው፡፡
ጦሩ ባለበት የጦር መሳርያ እና የተተኳሾች እጥረት የተነሳ ባልተሟላ ትጥቅ ወደ ፍልሚያ የሚገቡ ወታደሮች የቅርብ ጓዶቻቸውን በውግያ ላይ በሞት ማጣታቸው ትዕዛዝን እንዳይቀበሉ አድርጓቸዋል ተብሏል፡፡
በሁለቱ ተዋጊዎች መካከል የሚገኘው የወታደር ቁጥር አለመመጣጠን ደግሞ ሌላው ፈተና ነው፡፡
አዋጊዎቹ የጦሩን መሰላቸት ለመቀነስ በአራት እና በአምስት ቀናት ወታደሮችን ለማቀያየር ሙከራ ቢያደርጉም በውግያ ቦታዎች የሩስያ ድሮኖች ጥቃት መጨመር በአንድ ምሽግ ውስጥ እስከ 20 ቀናት እንዲቆዩ አስገድዷል፡፡
የዩክሬን ፓርላማ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በ2024 የመጀመርያዎቹ አራት ወራት ብቻ ከጦር ሜዳዎች ላይ በከዱ 19 ሺህ ወታደሮች ላይ በሀገር ክህደት ክስ ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው፡፡
የጦር መሪዎች ወታደሮች በሚያሳዩት ተስፋ መቁረጥ ፣ የውግያ ሞራል መቀነስ እና የበላይ ትዕዛዝን አለመቀበል ጥፋቶች ወታደሮች ተቀጥተው ወደ ውግያ ከሚገቡ ይልቅ፤ በማበረታቻ እና ተግሳጽ ሞራላቸውን ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ውጤታማ እንዳልሆነ ሲኤንኤን ያነጋገራቸው አዋጊዎች ተናግረዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የጦራቸው ግስጋሴ የሉሀንስክ እና ዶኔስክን ክልሎችን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር አላማ ያደረገ እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ የዩክሬን ጦር ዋነኛ የሎጂስትክ ማሳለጫ የሆነችውን ፖክሮቨስክን መቆጣጠር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡