የምዕራባውያን የጦር መሳርያ ድጋፍ መዘግየት ዩክሬንን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ ነው- ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ
ፕሬዝዳንቱ በምስራቅ ዩክሬን ከሚገኙ ብርጌዶች ግማሽ ያህሉ መሳርያ ያልታጠቁ መሆናቸውን ተናግረዋል
ፖክሮቨስክ አቅራቢያ ሩስያ በርካታ ስፍራዎችን በመቆጣጠር ላይ እንደምትገኝ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ አልሸሸጉም
ምዕራባውያን ለዩክሬን የሚያደርጉት ጦር መሳርያ ድጋፍ በመዘግየቱ የሀገሪቱ ጦር ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንት ቮለደሚር ዘለንስኪ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከሰሞኑ ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንዳሉት የጦር መሳርያዎቹ በአስፈላጊው የውግያ ግምባር በቶሎ ባለመድረሳቸው ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ከመሆኑም በላይ የሩስያ ጦር ግስጋሴ እንዲፋጠን አድርጓል።
በምስራቅ ዩክሬን ዋነኛ የጦር መሳርያ እና ሎጂስትኪ ማሳለጫ በሆነችው ፖክሮቨስክ አቅራቢያ ሩስያ በርካታ ስፍራዎችን በመቆጣጠር ላይ እንደምትገኝ ያልሸሸጉት ፕሬዝዳንቱ በዚህ አካባቢ ሌላ የጥቃት ዘመቻ መክፈቷን ተናግረዋል።
በምስራቅ ዩክሬን የሚገኝው ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸው በስፍራው ከሚገኙ ብርጌዶች ግማሽ ያህሉ ትጥቅ ያልታጠቁ ናቸው ብለዋል።
በተጨማሪም “በርካታ ወታደሮችን አጥተናል ምክንያቱ ደግሞ በአካባቢው የሚዋጉ ወታደሮች ጥይት መከላካያ የተገጠመለት ተሸከርካሪ የላቸውም ፣ የመድፍ እና የሌሎች የከባድ መሳርያዎች ተተኳሽ እጥረቱም ከፍተኛ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት ቃል የገቧቸው የጦር መሳርያ ድጋፎች መዘግየቱን ያነሱት ዘለንስኪ እነዚህን ድጋፎች በመጠቀም ትጥቅ ለመታጠቅ ተዘጋጅተው የነበሩ 14 ብርጌዶች በከፍተኛ የጦር መሳርያ እጥረት መስዕዋትነት እየከፈሉ መሆናቸውን ነው ያመላከቱት።
ፕሬዝዳንቱ የረጀም ርቀት ሚሳኤሎች የጦርነቱን ውጤት በመቀየር በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ባነሱበት ንግግር፤
“ቭላድሚር ፑቲን የሚያስፈራቸው ብቸኛው ጉዳይ የህዝብ ቁጣ ነው በረጅም ርቀት ሚሳኤሎች በሩስያ ውስጥ ኢላማዎችን ማጥቃት ብንጀምር የሚፈጠረውን ጉዳት ተከትሎ በሚኖረው የህዝብ ቁጣ ፑቲን ለውይይት ሊቀመጡ እንደሚችሉ እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫኒ መንግስት ለኪቭ በመጠኑ ከፍ ያለ የጦር መሳርያ ድጋፍ ለማድረግ እየተወያየ እንደሚገኝ ይፋ አድርገዋል።
አሜሪካ በቅርቡ ከ200 ሚሊየን ዶላር በላይ ግምት ያላቸው የጦር መሳርያዎችን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን ድንገተኛ ጥቃት በከፈተችበት የሩስያው ከርሰክ ግዛት በመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ወደ ኋላ እያፈገፈገች እንደምትገኝ መረጃዎች እየወጡ ነው።