የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ የጣለው ማዕቀብ ሞስኮን ብቻ መጥቀሙ ተገለጸ
የቀድሞው የቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕቀብ የሩሲያን ገቢ እያሳደገ ነው ብለዋል
የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ ለዘጠነኛ ጊዜ ማዕቀብ ጥሏል
የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ የጣለው ማዕቀብ ሞስኮን ብቻ መጥቀሙ ተገለጸ፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጠርነት ካመራች ከ10 ወራት በላይ ተቆጥረዋል፡፡
ይህ ጦርነት በሁለቱ ሀገራት ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ባለፈ የዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋን በማናር ለዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ምክንያት ሆኗል፡፡
በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት የሚመሩ ሀገራት በሩሲያ ላይ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦችን የጣሉ ሲሆን ሩሲያም ተመሳሳይ የአጸፋ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች፡፡
ቤልጂየምን ከፈረንጆቹ 1999 እስከ 2008 በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ገይ ቬርሆፍስታድት የአውሮፓ ህብረት በሞስኮ ላይ የጣለውን ማዕቀብ በትዊተር ገጻቸው ተችተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል ሆነው በማገልገል ላይ ያሉት ቬርሆፍስታድት ፥ ሩሲያ በተጣሉባት ማዕቀቀቦች ምክንያት የደረሰባት ጉዳት እንደሌለ ገልጻዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ የጣላቸው ማዕቀቦች በሞስኮ ላይ ያደረሱት ጉዳት ከዜሮ በታች ነው ብለዋል፡፡
ማዕቀቡ ለሞስኮ ተጨማሪ ገቢን እና ሽልማትን አስገኘላት እንጂ የጎዳት ነገር የለም ያሉት እኝህ ፖለቲከኛ፡ ሩሲያ ለከፈተችብን ጦርነት የሰጠነው ምላሽ የገቢ እና ወጪ ንግዷን አስፍቶላታል ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ በጣለው ማዕቀብ ምክንያት የሞስኮ ዓመታዊ እድገት በ3 ነጥብ 4 በመቶ ቅናሽ እንደሚያስመዘግብ ከዚህ በፊት ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዳይጎዷት የንግድ ልውውጧን ከዶላር እና ዩሮ ይልቅ ወደ ሩብል ማዞር፣ አዳዲስ እና ሰፊ ህዝብ ካላቸው ሀገራት ጋር የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነትን ማስፋት እንዲሁም የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማስፋት ላይ እንደምታተኩር መገለጿ አይዘነጋም፡፡
ሞስኮ ከአውሮፓ እና አሜሪካ ጋር የነበራትን የንግድ ግንኙነት በመቀነስ ከቻይና፣ ኢራን፣ ሕንድ እና ሌሎች የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ በማሳደግ ላይ መሆኗን አስታውቃለች፡፡