ምዕራባውያን ፑቲን ያቀረቡትን የሰላም እቅድ ውድቅ አደረጉ
የብሪታንያ፣ ጣሊያንና ጀርመን መሪዎች በሩሲያው ፕሬዝዳንት የቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች ፍጹም ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው ብለዋል
በስዊዘርላንድ ትናንት የተጀመረው የዩክሬን የሰላም ጉባኤ ዛሬም ቀጥሎ ይካሄዳል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም ያቀረቡት ቅድመ ሁኔታ በምዕራባውያን ሀገራት መሪዎች ተቃውሞ ገጥሞታል።
የዩክሬን የሰላም ጉባኤ ትናንት በስዊዘርላንድ ሲጀመር የብሪታንያ፣ ጣሊያን እና ጀርመን መሪዎች የፑቲንን የሰላም አማራጭ አጣጥለውታል።
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ፥ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ሀሳብ “ዩክሬናውያን ከዩክሬን ይውጡ እንደማለት የሚቆጠር ተራ ፕሮፖጋንዳ” ነው ብለዋል።
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝም እቅዱን “አምባገነናዊ ሰላም” ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በበኩላቸው የሩሲያው ፕሬዝዳንት ለድርድር ሃቀኛ ፍላጎት እንደሌላቸው ማሳየታቸውን ቀጥለዋል ሲሉ መደመጣቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከስዊዘርላንዱ የሰላም ጉባኤ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በዩክሬን ጦርነት ለማቆም ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጣቸው ይታወሳል፤ ኬቭ ከአራቱ ሩሲያ በከፊል ከተቆጣጠረቻቸው ግዛቶች ወታደሮቿን ታስወጣ የሚልና የኔቶ አባልነት እንቅስቃሴዋን ታቁም የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎች።
ዩክሬን ግን ይህን ቅድመ ሁኔታ ሉአላዊነቷና የግዛት አንድነቷን ያላከበረ መሆኑን በመጥቀስ የፑቲን ቅድመ ሁኔታ ውድቅ አድርጋዋለች።
ከ90 በላይ ሀገራት እና አለማቀፍ መሪዎች እየተሳተፉበት ባለው የስዊዘርላንዱ የሰላም ጉባኤም አለማቀፉ ማህበረሰብ በአንድ ድምጽ ሞስኮን እንዲቃወምና ዘላቂ መፍትሄን እንዲያበጅ ጠይቃለች።
ሩሲያም ሆነች አጋሯ ቻይና ያልተሳተፉበት ጉባኤ ከሁለት አመት በላይ ያስቆጠረውን ጦርነት ያስቆማል የሚል ተስፋ እምብዛም አልተጣለበትም።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ግን “ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ አሁንም እድል እንሰጣለን፤ ጦርነቱን ለማስቆም የጋራ ጥረት ሊደረግ ይገባል” ብለዋል።
አለማቀፉ ማህበረሰብ የተስማማበትን የሰላም እቅድ ለሩሲያ መንግስት ለማቅረፍ ዝግጁ መሆናቸውንም ነው ያነሱት።
ፕሬዝዳንቱ ከሩሲያው አቻቸው ጋር ፊት ለፊት ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ግን በንግግራቸው አልጠቀሱም።