የቡድን 7 አባል ሀገራት እንዳይንቀሳቀስ ከታገደው የሩስያ ገንዘብ 50 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን እንዲሰጥ ወሰኑ
ንብረትነቱ የሩስያ ማዕከላዊ ባንክ የሆነ በአውሮፓ ሀገራት እና በአሜሪካ የሚገኝ 300 ቢሊየን ዶላር እግድ እንደተጣለበት ይታወሳል
በጣሊያን ዛሬ የሚጀመረው የቡድን 7 አባል ሀገራት ጉባኤ በቻይና፣ ዩክሬን እና ጋዛ ጉዳይ ይመክራል
የቡድን 7 አባል ሀገራት ሩስያ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ካላት እንዳይንቀሳቀስ ከታገደው ገንዘብ 50 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን በብድር መልክ እንዲሰጥ ወስነዋል፡፡
በጣሊያን እየተደረገ በሚገኝው ጉባኤ ውሳኔውን ያሳለፉት አባላቱ የሩስያ ማዕከላዊ ባንክ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ያስቀመጠው 300 ቢሊዮን ዶላር ካስገኘው ወለድ ላይ ነው ገንዘቡ ለኬቭ እንዲሰጣት የወሰኑት፡፡
በገንዘቡ አሰጣጥ ዙርያ ዝርዝር ጉዳዮች ባይጠናቀቁም እስከ ፈረንጆቹ አመት መጨረሻ ድረስ ለዩክሬን ገቢ እንደሚደረግ ተነግሯል፡፡
ሞስኮ በኬቭ ላይ ጦርነት ማወጇን ተከትሎ በአውሮፓ ሀገራት የሚገኘው ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ በአሜሪካ እግድ ወጥቶበታል፡፡
ጦርነቱ በዩክሬን ላይ ያደረሰውን ጉዳት ለመቋቋም እና ለመልሶ ግንባታ ከሩስያ ገንዘብ ወጪ መደረግ አለበት በሚለው ጉዳይ ህጋዊ አካሄድ ላይ የአውሮፓ ሀገራት እና የአሜሪካ የህግ አዋቂዎች ለአንድ አመት ያክል ሲመካከሩ ቆይተዋል፡፡
ገንዘቡ እንዳይንቀሳቀስ ቢታገድም ንብረትነቱ የሞስኮ ማዕከላዊ ባንክ በመሆኑ በምን አይነት መንገድ ዩክሬን ከዚህ ገንዘብ ልትጠቀም ትችላለች የሚለው ጉዳይ ሲያወዛግብ ቆይቷል፡፡
የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫኒ ገንዘቡ ለዩክሬን መልሶ ግንባታ ፣ ለሀይል አቅርቦት ፣ ለኢኮኖሚ ድጎማ እና ለሌሎችም አስፈላጊ መንግስታዊ ወጪዎች ይውል ዘንድ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
ሩስያ የታገደባትን ገንዘብ ለማንቀሳቀስ ፈቃድ ባገኘችበት ጊዜ የተወሰደባት ገንዘብ በቦታው ካልተመለሰ አሜሪካ ለዩክሬን ዋስትና እወስዳለሁ ብላለች፡፡
የአለም ባንክ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት በሚቀጥሉት 10 አመታት ከ486 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ አመላክቷል፡፡
በጣልያኗ ፋሳኖ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄደው አመታዊው የቡድን 7 ጉባኤ ለዩክሬን ተጨማሪ ድጋፍ በሚደረግበት ሁኔታ እንዲሁም በቻይና ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ “ተስፋፊነት” ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይመክራል ተብሏል፡፡
ሰውሰራሽ አስተውሎት ፣ የህገወጥ ስደተኞች ጉዳይ እና የመካከለኛው ምስራቅ የጋዛ ጦርነት ተጨማሪ አጀንዳዎች ሆነው ቀርበዋል፡፡