ከሩሲያ ጋር እየዋጋች ያለችው ዩክሬን 152 ቢሊዮን ዶላር ጠቅላላ ብድር አለባት ተብሏል
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት በቀጠፈው እና ከሁለት አመት በላይ ባስቆጠረው ጦርነት ውስጥ ያለችው ዩክሬን የብድር ማስተካከያ ስራ ውስጥ ልትገባ ነው።
በፈረንጆች 2022 ሩሲያ የፈጸመችውን "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ተከትሎ በአፍጢሙ ተደፍቶ የነበረው የዩክሬን ኢኮኖሚ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከባለፈው አመት ጀምሮ መነቃቃት እያሳየ ቢሆንም ዩክሬን መጀመሪያ ላይ ያጋጠማት ድቀት የወለድ ክፍያ ለሁለት አመት ያህል እንዲቆምላት እንድትጠይቅ አስገድዷታል።
ዩክሬን የብድር ወለድ እንዳትከፍል የተፈቀደላት የሁለት አመት ጊዜ በመጭው ነሐሴ ስለሚጠናቀቅ፣ ዩክሬን የብድር ማስተካከያ ማድረግ፣ አበዳሪዎቿ ጊዜውን እንዲያራዝሙላት መጠየቅ ወይም ዲፎልት ወይም ብድር መክፈል የማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ለመግባት ጥቂት ጊዜ ይቀራታል ማለት ነው።
የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ሞስኮ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ እንዳይንቀሳቀስ ከተደረገው ከሩሲያ የውጭ ሀብት ወለድ የሚገኝ የ50 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ በትናንትናው እለት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ዩክሬን ከማን ተበደረች?፤ ምንያህልስ ተበደረች?
አጠቃላይ ብድር
እንደዩክሬን ፋይናንስ ማኒስቴር ከሆነ በዩክሬን መንግስት ዋስትና ሰጭነት የተገኘው ብደር በአጠቃላይ 152 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ይህ ጦርነቱ ከመጀመሩ ከሁለት ወራት በፊት ከነበረው የ98 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።
ሀገሪቱ አሁን ካለባት ብደር ውስጥ 70 በመቶ ወይም 108 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ብደር ሲሆን ቀሪው ደግሞ የመክፋያ ጊዜው ከ12 ወራት እስከ 30 አመታት የሆነ የሀገር ውስጥ ብድር ነው።
አሁን እየተካሄደ ያለው የብደር ማስተካከያ ጥረት የሚመለከተው ከአጠቃላይ የውጭ ብድር ውስጥ በንግድ ብደር ላይ ነው ተብሏል።
ዩሮ ቦንድ እና ዋራንትስ
ሀገሪቱ በዩሮ ቦንድ 19.67 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን የፋይናንስ ሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል። ሚያዝያ ወር ላይ በታተመው የጂፒ ሞርጋን ስሌት መሰረት ዩክሬን ወለድን ጨምሮ በዩሮ ቦንድ ያገኘችው ብደር አሁን ላይ 23.6 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል።
የተራዘመው መክፈያ ጊዜው የሚጠናቀቀው ነሐሴ መጨረሻ ሲሆን ባለቦንዶቹ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ሙሉ ክፍያ እንድትከፍል ስለማስገደዳቸው ግልጽ አልሆነም።
የኪቭ መንግስት በዚህ አመት መጀመሪያ አለምአቀፍ የግል አበዳሪዎቹ አንድ ቡድን እንዲያዋቅሩ እና በብድሮቹ ዙሪያ ድርድር እንዲደረግ ጠይቆ ነበር።
የመንግሰት ድርጅቶች ብድር
ዩክራቭቶዶር የተባለው የመንግስት የመንገድ ኤጀንሲ በመንግስት ዋስትና 700 ሚሊዮን ዶላር የተበደረ ሲሆን የሀገሪቱ የኃይል ተቋም ዩክሬነረጎ ደግሞ 830 ሚሊዮን ዶላር ብድር አለበት።
ለእነዚህ ሁለት ተቋማት ለሁለት አመት የሚቆይ ብደር የሰጡት ባለቦንዶች መክፍያ ጊዜው የሚጠናቀቀው በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ነው።
የሁለትዮሽ ብደር
ከካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ጀርመን፣ጣሊያን ጃፓን ኔዘርላንድስ ፖላንድ ብሪቴን እና አሜሪካ የተገኘው ብደር 7.5ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 5 ቢሊዮን በላይ ዶላሩ ከከናዳ የተገኘ ብድር ነው።
መልቲላተራል ብድር
ዩክሬን ካለባት የውጭ ብድር ውስጥ 70 ቢሊዮን ገደማ ወይም 2/3 የሚሆነው መልቲላተራል ብድር ነው። ከዚህ ውስጥ 16 ቢሊዮን ዶላሩ ከኢንተርናሽናል ሞናተሪ ፈንድ(አይኤምኤፍ) የተገኘ ነው።
ከባንኮች የተገኘ ብድር
ዩክሬን ከውጭ ባንኮች አጠቃላይ አንድ ቢሊዮን ዶለር ብድር ያለባት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 800 ሚሊዮን ዶላሩ ከቻይና ኢምፖርት-ኤክስፖርት ባንክ የተገኘ ነው።