ቱርክ "ሐሰተኛ መረጃ” በሚያሰራጩ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሚያስችላት ህግ አጸደቀች
አዲሱ ህግ “የሳንሱር ህግ” የሚል ስያሜ የሰጡት ተቺዎች አዋጁ የመናገር ነጻነትን የሚያፍን ነው ብለውታል
በቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋንን መሳደብ እስከ አራት አመት የሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ ይታወቃል
የቱርክ ፓርላማ “ሐሰተኛ መረጃ” በሚያሰራጩ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሚያስችል ህግ አጸደቀ፡፡
ፓርላመው ጸደቀው አዲስ የሚዲያ ህግ "የውሸት ዜና" ወይም "ሐሰተኛ መረጃን" በማሰራጨት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን እስከ ሶስት ዓመት የሚደርስ እስራት ለመቅጣት የሚያስችል ነው፡፡
ህጉ እያንዳንዳቸው የተለየ ድምጽ የሚያስፈልጋቸው 40 ማሻሻያዎችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡
ህጉ ሀሰተኛ ወይም አሳሳች መረጃ በማሰራጨት ጥፋተኛ ሆነው በተገኙ ሰዎች ላይ የወንጀል ቅጣት የሚያስቀጣ ሲሆን ማህበራዊ ድረ-ገጾች እና የኢንተርኔት ድረ-ገጾች "አሳሳች መረጃን በማሰራጨት" የተጠረጠሩ የተጠቃሚዎችን የግል ዝርዝሮች እንዲያስረክቡ ይጠይቃል።
የተቃዋሚ ህግ አውጭዎች እና የሚዲያ መብት ተሟጋቾች አዋጁ ውድቅ እንዲደረግ ቢጠይቁም የፓርላማ አብላጫ ድምጽ በድምሩ 333 መቀመጫዎች የያዙት የኤርዶጋን ገዥው ጀስቲስ ኤንድ ዲቨለፕምንት ፓርቲ (ኤኬፒ) እና ብሄራዊ ወዳጁ ናሽናል ሙቭመንት ፓርቲ (ኤም ኤች ፒ) አጽድቀውታል፡፡
ይሁን እንጅ የፓርላማው ውሳኔ በሀገሪቱ ዜጎች የመናገር ነጻነት ላይ ስጋት የሚፈጥር ነው በሚል እየተተቸ ነው ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
በተቺዎቹ “የሳንሱር ህግ” የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ ህግ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በምርጫ ለመዋዳደር ስምንት ወራት ሲቀራቸው የተደረገና መንግስት በመገናኛ ብዙሃን ላይና ሃሳብን በነጻነት የመገለጽ ላይ የሚደረግው ጥብቅ ቁጥጥር ያረጋገጠ እንደሆነም ይገለጻል፡፡
የኤርዶጋን መንግስት በጋዜጠኞች የሚያደርሰውን ጫና አጠናክሮ ለመቀጠል የወሰነው በምርጫው ወቅት ከኢኮኖሚ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በተያያዘ ሊነሱ የሚችሉ አጃንዳዎች ከወዲሁ ለማራቅ ነውም ብለዋል ተቺዎቹ፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቱርክ መንግስት በኦንላይን ይዘት እና በዲጂታል መተግበሪያዎች ላይ ያለውን ቁጥጥር በማጠናከር ከተቃዋሚ ጋር በተገናኙ የመገናኛ ብዙሃን የሚወጡትን ይፋዊ ማስታወቂያዎችን እና ማስታወቂያዎችን እየገታ ይገኛል።
በሀገሪቱ ህግ መሰረት ፕሬዝዳንቱን መሳደብ ከአንድ አመት እስከ አራት አመት የሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ ይታወቃል፡፡
ኤርዶጋን ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ወደ ፕሬዚዳንትነት ከተሸጋገሩ በኋላ ባሉት ስምንት ዓመታት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ፕሬዝዳንቱን በመሳደባቸው ለእስር ተዳርገዋል፡፡
ቱርክ በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር ከሚታወቁ የዓለም ሀገራት አንዷ ስትሆን በምዕራባውያን ሀገራት እና በመብት ተሟጋች ድርጅቶች በሰብዓዊ መብት አያያዝዋ ተደጋጋሚ ትችት ሲሰነዘርባት ይስተዋላል፡፡
የፕሬስ ነጻነት በማክበር ቱርክ ከ180 ሀገራት 149ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝም የድንበር የለሽ ጋዜጠኞች የዓለም የፕሬስ ነጻነት መረጃ ያመለክታል፡፡
በሀገሪቱ ውስጥ 90 በመቶው የመገናኛ ብዙሃን በመንግስት ቁጥጥር ስር ናቸው እንደሆኑም መረጃው ያክላል፡፡