“የአሜሪካ መቃወሚያዎች የኦሬሽኒክ ሚሳኤልን መቋቋም የሚችሉበት አቅም ካላቸው መሞከር ይችላሉ” -ፑቲን
የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አመታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ወቅታዊና ቀጠናዊ ጉዳዮችን አብራርተዋል
ምዕራባውያን ሚሳኤሉን መቋቋም የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንዳላቸው እርግጠኞች ከሆኑ በፈለጉት ኢላማ ላይ መሞከር እንደሚችሉ ፑቲን ተናግረዋል
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቅርብ ጊዜ በዩክሬን ላይ ያስወነጨፉትን “የኦሬሽኒክ” የባለስቲክ ሀይፐር ሶኒክ ሚሳኤል አስመልክቶ አነጋጋሪ ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡
ፑቲን “ምዕራባውያን እና አሜሪካ የኦሬሽኒክ ሚሳኤልን መቋቋም የሚችል የአየር መቃወሚያ ካላቸው በመረጡት ኢላማ ላይ ሙከራ ማድረግ ይችላሉ” ብለዋል፡፡
በአሜሪካ የሚሳኤል መከላከያ ስርአቶች የሚጠበቅ የትኛውም ኢላማ ተመርጦ የኦሬሽኒክ ሚሳኤልን መቋቋም መቻሉን ለማረጋገጥ ሙከራ ማድረግ ይችላሉ ነው ያሉት፡፡
ሞስኮ ባሳለፍነው ህዳር በዩክሬን ዲኒፕሮ ግዛት ከፍተኛ የማጥቃት አቅም ያለው፣ ለአየር እና ለሚሳኤል መቃወሚያ ስርአቶች ፈታኝ ነው የተባለውን “ኦሬሽኒክ” ሀይፐር ሶኒክ ሚሳኤል ለመጀመሪያ ጊዜ በጦርነት ላይ መጠቀሟ ይታወሳል፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን በአመታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው የትራምፕ መመርጥ እና ቀጣይ ስለሚኖር ግንኙነት፣ የዩክሬን ጦርነት፣ የሰላም ድርድር ፣ የሩስያ ኢኮኖሚ እና ሶሪያን የተመለከቱ ጉዳዮችን ዳሰዋል፡፡
ሶሪያን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር አሁን ላይ መንግስት ለመመስረት እየሞከሩ ከሚገኙ አካላት እና ከቀጠናው አጋሮች ጋር ግንኙነቱ መቀጠሉን ያስታወቁት ፕሬዝዳንቱ የሩስያ ወታደራዊ ካምፖች ባሉበት እንዲቀጥሉ ጥያቄ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም “ብዙዎች በሶሪያ ውስጥ እየተከሰተ ያለውን ነገር ሁሉ እንደ አንድ የሩስያ ውድቀት እና ሽንፈት መገለጫ አድርገው መሳል ይፈልጋሉ፤ ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው ነገር ግን ይህ ሀሳብ ትክክል አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ከትራምፕ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ዙርያ በሰጡት ማብራርያ ከተመራጩ ፕሬዝዳንት ጋር ከተነጋገሩ አራት አመታት እንደተቆጠሩ እና መቼ እንደሆነ ባላውቅም ከፕሬዝዳንቱ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ነኝ ብለዋል፡፡
የዩክሬንን ጦርነት በድርድር ለመቋጨት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንት ፑቲን “በጦርነቱ መዋጋት የሚፈልጉ ዩክሬናውያን ቁጥር እየቀነሰ ይመጣል፤ በእኔ አስተያየት ብዙም ሳይቆይ መዋጋት የሚፈልግ ሰው አይኖርም፤ እኛ ዝግጁ ነን ነገር ግን ሌላኛው ወገን ለድርድር እና ስምምነት ዝግጁ መሆን አለበት” ነው ያሉት።
በመጨረሻም ፕሬዝዳንቱ ከዳሰሷቸው ነጥቦች መካከል የሩሲያን ኢኮኖሚ የተመለከቱ ጉዳዮች ይገኙበታል፡፡
በዚህም ምንም እንኳን ውጫዊ ጫናዎች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጫና ለማሳደር ከፍተኛ ተጽዕኖ ቢያደርጉም ኢኮኖሚው በተረጋጋ ሁኔታ እየተጓዘ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
ሆኖም ፕሬዝዳንቱ እየጨመረ ስለሚገኘው የዋጋ ንረት አሳሳቢነት አልሸሸጉም፤ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋትም መንግስት እና ማዕከላዊ ባንክ በቅርበት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡