ፑቲን “የኦሬሽኒክ” ሚሳኤል በብዛት እንዲመረት አዘዙ
ከድምጽ ፍጥነት በአስር እጥፍ የሚጓዘው ኦሬሽኒክ የተባለው ሃይፐር ሶኒክ ሚሳኤል ለመጀመርያ ጊዜ ጥቅም ላይ ውሏል
ሚሳይሉ በደቂቃዎች ውስጥ አብዛኛውን አውሮፓ እና የአሜሪካ ምዕራባዊ የባህር ጠረፍ አካባቢን ማጥቃት የሚያስችል ነው
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አዲሱን “የኦሬሽኒክ” ባለስቲክ ሚሳኤል በጅምላ እንዲመረት ትዕዛዝ መስጠታቸውን ገለጹ፡፡
ሚሳይሉ በጅምላ እንዲመረት የታዘዘው በዚህ ሳምንት በዩክሬን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በውጊያ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ነው።
በክሬምሊን ከመከላከያ ሚኒስቴር አመራር እና ከመከላከያ ኢንዱስትሪ ተወካዮች ጋር በተደረገው ስብሰባ ላይ ፑቲን እንደተናገሩት “የኦሬሽኒክ” ሚሳኤል ስርዓት የሩሲያ የቅርብ ጊዜ ወታደራዊ ግስጋሴዎች ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ወቅታዊ የሩሲያ የመከላከያ ፍላጎትን ለማሟላት የተሰራ ነው የተባለው ሚሳይል በከፍተኛ የሃይፐርሶኒክ ቴክኖሎጂ እና በዘመናዊ ቁሳቁሶች ላይ ተመስርቶ የተመረተ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በርካታ “የኦሬሽኒክ” ሚሳኤሎች በሩሲያ ውስጥ በሙከራ ላይ መሆናቸውን ያረጋገጡት ፕሬዝዳንቱ የጅምላ ምርትን ለመጀመር አስቀድሞ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
በሚቀጥሉት ወራቶችም በርካታ የዚህ አዲስ ቴክኖሎጂ ውጤት ሚሳይሎች በሀገሪቱ ጦር መካዘን ውስጥ እንደሚቀላቀሉ እና ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ተናግረዋል፡፡
“የኦሬሽኒክ” ሚሳኤል ለመጀመርያ ጊዜ በውግያ ላይ ጥቅም ላይ የሰጠው ባሳለፍነው ሀሙስ ዕለት በዴንፕሮፔትሮቭስክ የዩክሬን መከላከያ ተቋምን ለመምታት ነው።
የጥቃቱ ኢላማ ከቀድሞ ሶቭየት ህብረት የተወረሰው የሚሳኤል መሳሪያዎችን እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን የሚያመርት የዩክሬን ትልቁ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ተቋማ ላይ አነጣጥሯል፡፡
የ“የኦሬሽኒክ” ሚሳይል ልዩ መገለጫዎች ምንድን ናቸው?
የሃይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳይል እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ሚሳይል ከድምጽ ፍጥነት 10 እጥፍ ፍጥነት መጓዙ በሚሳይል መቃወሚዎች ለማክሸፍ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
5000 ኪ.ሜ ድረስ የሚጓዘው የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤል በደቂቃዎች ውስጥ አብዛኛውን አውሮፓ እና የአሜሪካ ምዕራባዊ የባህር ጠረፍ አካባቢን ማጥቃት የሚያስችል ነው፡፡
ከአንዱ ሚሳይል ውስጥ የሚወጡ የጦር አረሮች በአንድ ጊዜ በርካታ ኢላማዎችን ማጥቃት የሚችሉ ሲሆን ከ6-8 ኒውክሌር መሸከም የሚችሉ የጦር አረሮችን መያዝ እንደሚችልም ተነግሮለታል፡፡
ከሩሲያ ጀርመን ለመድረስ 14 ደቂቃ ብቻ እንደሚበቃው የተነገረለት “ኦሬሽኒክ” በ40 ደቂቃዎች ውስጥ በአሜሪካ ያሉ ኢላማዎችን መምታት እንደሚችል ተገልጿል።
ከሩሲያ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል እንደተተኮሳባት የተናገረችው ዩክሬን አለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህን መሳርያ ጥቅም ላይ እንዳይውል ጫና እንዲያሳደሩ በመጠየቅ ላይ ትገኛለች፡፡